በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አበረታች ውጤት መመዝገቡን የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አበረታች ውጤት መመዝገቡን የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 02/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአብዛኛው ዘርፎች አበረታች ውጤት መመዝገቡን የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ገለጹ።

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት 4ኛ ዙር 12ኛ ዓመት 29ኛ መደበኛ ጉባኤ የ2018 በጀት አመት ስራ ማስፈፀሚያ በጀት 7 ቢሊየን 48 ሚሊየን 395 ሺህ 502 ብር አድርጎ አጽድቋል።

የዞኑ ምክር ቤት 4ኛ ዙር 12ኛ ዓመት 29ኛ መደበኛ ጉባኤ በወልቂጤ ከተማ እየተካሔደ ነው፡፡

‎የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ ኸይሩ መሃመድ ጉባኤውን በከፈቱበት ወቅት እንዳሉት ሃገሪቷ ባለፉት 7 የለውጥ አመታት በርካታ ፈተናዎች የገጠሟት ቢሆንም ፈተናዎቹን በጥበብ በመቋቋምና የሪፎርም ስራዎችን በመስራት በሠላም፣ በዲሞክራሲ፣ በልማትና በመልካም አስተዳደር ዘርፎች ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል።

‎በዚህም በከተሞች መሠረተ ልማት ከማስፋፋት በተጨማሪ ከተሞችን ፅዱ ማራኪና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ በተሠሩ ሥራዎች ለውጥ መታየቱን ጠቁመው፥ እንደ ዞን በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጠሩ ያሉ የፀጥታ ችግሮች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ለመፍታት እየተሠራ እንደሚገኝም አቶ ኸይሩ አስረድተዋል።

‎በመሠረተ ልማት ዘርፍ ማህበረሠቡ የተለያዩ በጎ አድራጊ ድርጅቶችና ባለሀብቶች ከመንግስት ጋር በመተባበር በርካታ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን ገልፀዋል።

‎የዞኑ አስተዳደር ምክር ቤት የ2017 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት መነሻ በማድረግ ከምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎችን አንስተዋል።

‎ሠላም ከማስፈን ጋር ተያይዞ ማህበረሠቡን በማወያየትና የጋራ አቋም በመያዝ የታዩ ለውጦች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተመላክቷል።

ወልቂጤ ከተማን ከአቻ ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ ለማድረግ እየተሠሩ ያሉ ስራዎች ተስፋ ሠጪ መሆናቸው ያመላከቱት አባላቱ፥ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ይበልጥ ለማጠናከር ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

‎የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠሩ የሚገኙ ሥራዎች ጠንካራ መሆናቸው በመጠቆም የቡና ምርትን ከማሳደግ ጋር ተያይዞ ይበልጥ መሥራት እንደሚጠይቅ ገልጸው፥ የወልቂጤ ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሀ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መሠራት እንዳለበትም አመላክተዋል።

በሁሉም ዘርፍ የሴቶችን አቅም ለማሳደግ ጠንካራ ሥራ መሥራት ተገቢ መሆኑንም አንስተዋል የምክር ቤቱ አባላት።

‎የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየት በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፥ በተጠናቀቀው በጀት አመት በአብዛኛው ዘርፎች አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸው፥ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንደአስፈላጊነተቸው ደረጃ በደረጃ ምላሽ ይሰጣቸዋል ብለዋል።

ከግብርና ልማት ጋር ተያይዞ በሌማት ትሩፋት፣ በተፋሠሥና በሌሎችም ዘርፎች የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ ተግባራቱ ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው።

‎በዞኑ በባህር ዛፍ የተያዙ መሬቶች በ2018 በሌሎች የምግብ ሠብሎች በሥፋት እንደሚለሙ የገለጹ ሲሆን፥ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት የ2018 በጀት አመት ስራ ማስፈፀሚያ በጀት 7 ቢሊየን 48 ሚሊየን 395 ሺህ 502 ብር ሆኖ እንዲጸድቅ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ አድቋል።

ዘጋቢ፡ እቴነሽ ቲሬቦ – ከወልቂጤ ጣቢያችን