በትምህርት ለትውልድ ከ182 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

በትምህርት ለትውልድ ከ182 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 01/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዳውሮ ዞን በትምህርት ለትውልድ መርሃ ግብር ከ182 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል።

ለተማሪ ውጤትና ሥነ ምግባር መሻሻል የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ በቅንጅት ሊሠራ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ገልጿል።

“የጋራ ርብርብ ለላቀ የትምህርት ጥራት” በሚል መሪ ቃል የባለ ድርሻ አካላትን ያሳተፈ
ዞናዊ የትምህርት ንቅናቄ መድረክ በታርጫ ከተማ ተካሂዷል።

ካለፉት ጥቂት ዓመታት ጀምሮ በትምህርት ጥራት መሻሻል ላይ አገራዊ ግብ ተጥሎ እየተሠራ ሲሆን፥ በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት ተቋማት ለዘርፉ ውጤታማነት በተቀናጀ ርብርብ ተግባራቸውን እየተወጡ ነው።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊ ዶክተር ደስታ ገነሞ እንደገለፁት የትምህርት ዘርፍ ውጤታማነት እንዲረጋገጥ ለማድረግ የባለ ድርሻ አካላትን በማሳተፍ ተግባሩ በትኩረት እየተመራ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ዞኖች የጋራ ርብርብ ለላቀ የትምህርት ጥራት በሚል መሪ ቃል የንቅናቄ መድረኮች ለ2018 የትምህርት ዘመን ውጤታማነት እየተካሄደ መሆኑ ተመላክቷል።

በዳውሮ ዞን በተለይ በብቃት፣ በጥራትና በተነሳሽነት የትምህርት ስብራትን መጠገን እንዲቻል የማሳኪያ ንድፎች ቀርበው ተግባራዊ እንዲሆኑ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የንቅናቄ መድረክ መካሄዱን የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታማኝ ኃይሌ ገልጸዋል።

በዞኑ ባለፉት ዓመታት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን አስፈትነው ወደ ዩኒቨርሲቲ ያላስገቡ ትምህርት ቤቶችን በመለየት የድጋፍና ክትትል ተግባር እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።

75 ከመቶ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች በመሆናቸው ምቹ የመማሪያ ሂደት እንዲፈጠር የትምህርት አምባሳደር የመመደብ ተግባር በመከናወን ላይ ይገኛልም ብለዋል።

የዞኑ የመንግሥት ዋና ተጠሪና የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታሪኩ አካሉ በንቅናቄው መድረክ እንደገለፁት ለትምህርት ጥራት መሻሻልና ውጤታማነት መረጋገጥ ለዘርፉ የሚደረገው ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ትኩረት ሊደረግ ይገባል።

ለትምህርት ውስጣዊ ጥራት፣ በመጠነ ማቋረጥና መጠነ መድገምን ለመቀነስ ሊሠራ ይገባል ያሉት ኃላፊው፥ በተጠናቀቀው የትምህርት ዘመን 60 ከመቶ የነበረውን የተማሪ ቅበላ አቅም ከፍ ለማድረግ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

አገራዊ ኢንሼቲቭ የሆነው “በትምህርት ለትውልድ” መርሃግብር የገቢ ማሰባሰብ ሂደትን አጠናክሮ በማስቀጠልና የውስጥ ገቢን አሟጥጦ በመሰብሰብ ለትምህርት ግብኣት መሟላትና በትምህርት ቤቶች የደረጃ ማሻሻያ ላይ ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል።

በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ከ182 ሚሊዮን በላይ ብርና ለዳዉሮኛ ቋንቋ መፃሕፍት ሕትመት ይሆን ዘንድም 32 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱም ገልጸዋል።

ለትምህርት ጥራት መሻሻል የራሳቸውን ድርሻ እንደሚወጡ አስተያየታቸውን ከሰጡ ተሳታፊዎች መካከል በዞኑ ትምህርት መምሪያ የትምህርት ቤቶች ማሻሻል ቡድን መሪ አቶ ዮሐንስ ብርሃኑና በታርጫ ከተማ አስተዳደር የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሱፐርቫይዘር መ/ር ሁሴን ከበደ ይገኙበታል።

የተማሪዎች የቅበላ አቅም ከፍ ለማድረግ የተቀናጀ ርብርብ ይደረጋልም ብለዋል።

በዞኑ በ2018 የትምህርት ዘመን በ440 ትምህርት ቤቶች ከ211ሺህ 462 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተምር በእቅዱ አመላክቷል፡፡

ዘጋቢ፡ መሣይ መሠለ – ከዋካ ጣቢያችን