የስም ነገር

የስም ነገር

በአንዱዓለም ሰለሞን

የሆነ ቀን ምሽት፡፡ ከአዲሱ መናኸሪያ ወደ ቤቴ እየሔድኩ ነበር፡፡ ቀኜን ይዤ በእግረኛ መንገድ እያዘገምኩ፣ በዛውም ባጃጅ ካገኘሁ በሚል በዐይኔ እያማተርኩ፡፡ እንደእኔው ከፊት ለፊቴ የምታዘግም ልጅ ሁለት ባጃጆች አልፈውን መሔዳቸውን ካስተዋለች በኋላ፡-

“ባጃጅ አይገኝም?” አለችኝ፡፡

“እየሔድን እንጠብቃለና” አልኳት፡፡

እየሔዱ መጠበቅ፣ ጉዞን ሳያቆሙ አማራጭ መፈለግ፡፡ ይህ የህይወት ጉዞ ምሳሌ ነው፡፡ ነገን ተስፋ እያደረጉ ዛሬን መኖር። በመኖር ውስጥ ደግሞ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ አንዳንዴ አለመኖርም ይኖራል፡፡ አለመኖርን አሸንፎ ለመኖር ታዲያ ተስፋ ያስፈልጋል። ከተስፋ ባሻገር ደግሞ የሆነ የሚኖሩለት ነገር፣ ይህ ነው የሚሉት ሁነኛ ዓላማ! …

“ከስራ ከወጣሁ በኋላ ጓደኛዬ ዘንድ ሄጄ ዝናብ ያዘኝና ሳላስበው መሸ” አለች፡፡

እኔንም ያጋጠመኝ መሰል ነገር ነበር፡፡

“የት ነው ሰፈርሽ?” ስል ጠየኳት።

“ሞቢል፡፡”

“እንደዛ ከሆነ እኔን እስከወልደ አማኑኤል ትሸኚኝና እዛ ጋ ወደ አሮጌው መናኻሪያ የሚሄድ ታክሲ አታጭም” አልኳት፡፡

“እኔን ሸኝኚና ተመቸኝ” አለች እየሳቀች።

ከሁኔታዬ ለመግባባት የማይከብድ ዓይነት ሰው እንደሆንኩ እንዳሰበች ገመትኩ። ስንተዋወቅ “ገነት” ስትል ስሟን ነገረችኝ። የእኔን ስም ከነገርኳት በኋላ፡-

“ስለስምሽ ትርጉም ግን አስበሽ ታውቂያለሽ?” ስል ጠየኳት፡፡

“ማለት?”

“ወይም ደግሞ ጥያቄዬን ላሻሽለው” አልኩና፡-

“ገነት ማለት ላንቺ ምን ይመስልሻል? ማለቴ ስለገነት ስታስቢ ምንድነው በአእምሮሽ የሚመጣው?” ስል ጠየኳት፡፡

“አይገርምም አንድም ቀን አስቤው የማላውቀውን ጥያቄ ነው የጠየቅከኝ” አለች ፈገግ ብላ፡፡

እርግጥ ነው የስሟ ትርጉም የእሷ ብቻም ሳይሆን ማንም ስለገነት መኖር የሚያምን ሀይማኖተኛ ሰው ጥያቄ ነው፡፡ የእሷን ልዩ የሚያደርገው ግን የስሟ ስያሜ መሆኑ ነው። ግን ደግሞ አስባው አታውቅም፡፡

“አንተ ምን ታስባለህ?” ስትል ጠየቀችኝ።

“ገነት ለእኔ አያቴ ያለችበት ቦታ ይመስለኛል፤ አያቴ እና መሰል ሰዎች የሚኖሩበት” አልኳት። ሳቅ አለችና፡-

“ለምን እንደዚህ አልክ?” ስትል ጠየቀችኝ።

“አያቴ ሰውን የሚጎዳ ነገር ስታደርግ አይቻት ስለማላውቅ፣ ባልንጀራህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ እና በፍቅሬ ኑሩ የሚሉትን የሀይማኖቷን ትዕዛዛት አክብራ ስለኖረች” አልኳት፡፡

“በዚያ ነው እርግጠኛ የሆንከው?”

“ሲጀመር ይመስለኛል እንጂ እርግጠኛ ነኝ አላልኩም፡፡ ሲቀጥል ከዚህ በላይ ምን አለ፤ አያቴ እነዚህን ህጎች ስለጠበቀች ከብዙ ነገሮች ታቅባለች፡፡ ሙስና አልበላችም፣ አላጭበረበረችም፣ ሰውን በብሔር ወይም በሀይማኖት ለይታ አልበደለችም፣ አላዳላችም፣ የሰው ደም በከንቱ አላፈሰሰችም” አልኳት እየሳቅሁ፡፡

አብራኝ ስትስቅ ቆየችና፡-

“ይገርማል!” አለች፡፡

“ምኑ?”

“ለአያትህና ለገነት ያለህ እሳቤ፡፡”

ይህን ካለች በኋላ፡-

“እስቲ እኔም አስብበታለሁ” አለች፡፡

“አንቺማ በደንብ አስቢበት እንጂ የስምሽ መጠሪያ አይደል እንዴ!” አልኳት፡፡ ይህን ስላት ወልደ አማኑኤል አደባባይ ደርሰን ነበርና ታክሲ መቆሚያው ጋ ቆምን፡፡

“እኔ ደርሻለሁ፡፡ ታክሲ ላሳፍርሽና እንለያይ” አልኳት፡፡ ብዙም ሳይቆይ ታክሲ መጣ፡፡ ስለሸኘኸኝ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ጥሩ ሰው ነህ” አለችኝ ወደታክሲው ስታመራ።

“ሲጀመር አንቺ ነሽ የሸኘሽኝ፡፡ እኔ ሰፈሬ ደርሻለሁ፡፡ ጥሩ ሰው የምባለው ግን እንደአያቴ ብሆን ነበር” አልኳትና፡-

“ለማንኛውም መልካም ጊዜ” ብያት ተሰነባብተን ተለያየን፡፡

ታክሲ ውስጥ ሆና ስለስሟ ማሰቧ እንደማይቀር እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ እኔም ወደቤቴ ሳዘግም ከዚሁ የራቀ ሀሳብ አልነበረኝም፡፡

እኔ ‘ምለው፤ ሰው እንዴት ለልጁ “አሸብር” የሚል ስም ያወጣል፡፡ አሸብር ያለው ልጅ አሸባሪ ቢሆን ያማርር ይሆን?

“ዝም አርጋቸው” ያልከው ልጅህ አይበለውና ባለስልጣን ቢሆን የሚዲያ ብቻም ሳይሆን የማውራት ነጻነት ጭምር እኮ ነው የሚነፍገን ጎበዝ! “ግዛቸው” የተባለው ልጅንስ ማነው ስልጣን በቃህ የሚለው፤ ከልጅነቱ ጀምሮ ሰፈርም ትምህርት ቤትም በዚህ ስም ሲጠራ ኖሮ፡፡

እርግጥ ነው፤ አንዳንዴ ስም ግብርን ላይገልጽ ይችላል፡፡ አሁን ለምሳሌ አንድ “አሸብር” የተባሉ ዘመድ አሉኝ፡፡ መነኩሴ ናቸው፡፡ ደግነቱ መነኩሴ በዓለማዊ ስሙ አለመጠራቱ በጀ እንጂ አሸብር ተብሎ የሚጠራን መነኩሴ አስባችሁታል?

ይህም ሆኖ ግን፣ ብዙ ጊዜ ሚዲያ ላይ የማይጠፉት አባ… አንዳንድ ያየሁባቸውና የሚናገሯቸው ነገሮች አሸብርነታቸው ከምንኩስናቸው ይጎላል እንዴ ስል እንዳስብ አድርጎኝ ያውቃል፡፡

በሀገራችን “ስምን መልአክ ያወጣዋል” የሚል አባባል አለ፡፡ እኔ ግን እላችኋለሁ፣ አሁን “አናጋው” የሚለውን ስም መልአክ ነው ያወጣው? እንኳን መልአክ ወላጅ ማውጣቱ ራሱ አስገራሚ ነው፡፡ “ጎንጤ” እና “አዝብጤ” የሚሉትንም እንደዛው፡፡

አንዳንድ ስሞች ደግሞ በምክንያት ይወጣሉ፡፡ እነዚህ ስሞች ታዲያ ለወላጅ የትዝታ ምክንያት ሆነው ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ አጎቴ እናቱ የሞተች ሰሞን የተወለደች ሴት ልጁን “እናቴነሽ” ሲል ስም አወጣላት። በዚህ የተነሳ በእድሜ ዘመኑ የልጁ ስም እናቱን እንዳስታወሰው ይኖራል ማለት ነው፡፡

አንዳንድ ስሞች ደግሞ ከአባት ስም ጋር ሲጠሩ ትርጉም ይሰጣሉ፡፡ ለምሳሌ መሰረት ይሁን እንደሚለው እንደ አንድ ጓደኛዬ ስም ዓይነት፡፡ እያደር አዲስ፣ ስመኘው በቀለ፣ ይገደብ ዓባይ፣ ዓባይ ሞላ፣ የ በረከት የሚሉት ዓይነት ስሞችን ማለቴ ነው፡፡ እዚህ ላይ ታዲያ ጥምረቱ ከዚህ በተቃራኒው የሆነ ትርጉም የሚፈጥር ስያሜም ስለሚኖር፣ የፈለገ ስሙን ብንወደው እንኳ የማንሰይመው ስም ይኖራል፡፡ ለምሳሌ “ደረሰ” የተባለ ሰው ስሙን ምን ቢወደው ለሴት ልጁ “ሳራ” የሚል ስም ማውጣት አይችልም፤ ወይ የእሱን ስም ካላስቀየረ በቀር፡፡

እዚህ ላይ የሚነሳው ሌላው ነገር፣ አሁን አሁን የልጆቻቸው ስም ነገር ብዙ ወላጆችን ሲያስጨንቃቸው እየታዘብን ነው፡፡ ይህ መሆኑ ምንም ችግር ላይኖረው ይችላል፡፡ ግን ደግሞ፣ ለስማቸው የተጨነቁትን ያህል ላስተዳደጋቸው የማይጨነቁ ከሆነ ነው ችግሩ፡፡

“ቅጣው” ብለህ የሰየምከውን ልጅህን በአግባቡ ቀጥተህ ካላሳደከው፣ ሲያድግ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስቀድሞ ማሰቡ ይጠቅማል፡፡ “አስማማው” ያልከውን ልጅህንም እንዲሁ ገና በልጅነቱ ከጓደኞቹ ጋር ተስማምቶ እንዲኖር ካላደረከው ስሙን መሰየሙ ብቻ ዋጋ አይኖረውም፡፡

“ነገርን ነገር ያነሳዋል” እንዲሉ፣ የራሴው ነገር ትዝ አለኝ፡፡ አንድ ጊዜ አንድ ጓደኛዬ፡-

“የልጅህን ስም ናታን ብለህ የሰየምከው ለምንድነው” ሲል ጠየቀኝ፡፡

“ናታን ዳዊትን በሳተ ጊዜ እንደገሰጸው ታውቃለህ አይደል?” አልኩት፡፡ በሀሳቤ መስማማቱን ለመግለጽ ጭንቅላቱን ነቀነቀ፡፡

“እኔም ልጄ መገሰጽ ያለባቸውን እንዲገስጽ ብዬ ነው” አልኩት እየሳቅሁ፡፡ እሱም አብሮኝ ሲስቅ ከቆየ በኋላ፡-

“ጥሩ፣ ለማንኛውም መጀመሪያ የሰፈር ሰው እንዲያከብር አንተ መጀመሪያ ገስጸህ አሳድገው” አለኝ፡፡

እርግጥ ነው፤ እውነታው ይህ ነው። ስም ለማውጣት ከመጨነቃችን ባሻገር፣ ልጆቻችንን በአግባቡ ለማሳደግ የምናደርገው ነገር ነው ምግባራቸውን እንደስማቸው የሚያደርገው፡፡ ያ ካልሆነ ግን፣ ተስፋዬ ያልከው ልጅ ተስፋ ያስቆርጥሀል፡፡ ሚሊዮን ብለህ የሰየምከው እንኳንስ ሰርቶ ሀብት ሊፈጥር ይቅርና፣ ያንተንም ጥሪት አውድሞ መቀመቅ ይከትሀል፡፡  ደረጀ ያልከው መልሶ ያንተው ጡረተኛ ይሆናል፡፡ መሰረት ያልከው ወይንም ያልካት መሰረትህን ያናጉታል። በረከት ያልከው መቅኖቢስ ሆኖ ረድኤት ያሳጣሀል፡፡ …

እናም ለልጃችን “በድሉ” ብለን ስም ስናወጣለት፣ በእድሉ ብቻ እንደማያድግ ጭምር እያሰብንና ስለአስተዳደጉም ግድ እያለን ቢሆን ጥሩ ነው፤ “እድል” ወይም “እድላዊት” ብለን ስለሰየምናት ልጅም እንዲሁ፡፡