የመንግስት የልማት አጋር አካላት የሚያከናውናቸው ተግባራት ውጤት እንዲያስመዘግቡ ሊሰራ እንደሚገባ ተገለፀ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 01/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የመንግስት የልማት አጋር አካላት ለህዝቡ ለውጥ የሚያከናውናቸው ተግባራት በተደራጀ መልኩ ውጤት እንዲያስመዘግቡ በልዩ ትኩረት መሠራት እንዳለበት ተገለፀ።
በደቡብ ኦሞ ዞን የሚሠሩ የመንግስት የልማት አጋር አካላት በፕሮጀክቶች ክትትልና ግምገማ ዙሪያ የሚመክር የጋራ መድረክ በቱርሚ ከተማ ተካሂዷል ።
የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ ዞኑ ሰፊ የልማት ክፍተት ያለበት በመሆኑ ከመንግስት ጎን በመቆም የሚሠሩት የልማት አጋር አካላት ሚና ወሳኝ ነው ብለዋል።
ከዚህ በፊት የመንግስት የልማት አጋር አካላት ያከናወናቸው ሁሉ አቀፍ የልማት ሥራዎች የአካባቢው ማህብረሰብ እንዲለወጥ ትልቅ አቅም መፍጠሩን ዋና አስተዳዳሪው ገልፀው በቀጣይ ሰብሰብ ብሎ የተሻለ አቅም ፈጥሮ ተግባራትን መምራት ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል።
በመድረኩ በአካባቢው የሚሠሩ ከ30 በላይ የልማት አጋር አካላት 90 ያህል ከፌዴራል ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት የሥራ ሀላፊዎችና እና የክትትልና ግምገማ ባለሙያዎች ተገኝተው ምክክር አድርገዋል።
የሲቪክ ማህብረሰብ ተቋማት ሥራዎችን በምን አግባብ እየከወኑ እንዳሉ ግምገማ ማካሄድ፣ መደገፍና በጋራ ቅንጅት ለተሻለ ሥራ መተባበር እንደሚያስፈልግ በኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን በኩል በተካሄደ የመነሻ ጥናት ተመላክቷል፡፡
የጋራ መድረኩ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት መዘጋጀቱን የፋውንዴሽኑ የግብርና ትራንስፎርሜሽን የምግብና ሥነ-ምግብ ዋስትና ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ፈለሀ አስረድተዋል።
የሲቪክ ማህብረሰብ ተቋማት በየአካባቢው በተጠናጠል በሚሠሩበት ወቅት ሥራዎችን ቆጥሮ ለመገምገምና ጉድለቶችን ለይቶ ለማረም አመቺ ባለመሆኑ በቀጣይ የጋራ ቅንጅት መርሕ ላይ በመመስረት ተግባራትን መሥራት እንደሚያስፈልግና ለዚሁም ከመድረኩ በፊት ለተከታታይ ሦስት ቀናት ለመንግስት የክትትልና ግምገማ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱን አቶ ተስፋዬ አስረድተዋል።
መደጋገፍና ክፍተቶችን ተናቦ ለተሻለ ውጤት መብቃት ትልቅ ግብ ሆኖ እንዲቀጥል ይደረጋል ያሉት የደቡብ ኦሞ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ሀላፊ አቶ ምናሴ ዘውዴ ሲሆኑ፥ በቀጣይ በቅንጅትና በትብብር ልማታዊ ውጥኖችን መፈፀም ይጠበቃል ብለዋል።
የፌደራል የሲቪክ ማህብረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የመሠረታዊ አገልግሎት ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዳንኤል ግዛው የሲቪክ ማህብረሰብ ብቻቸውን የሚያከናውናቸው ተግባራት በሚጠበቀውና በሚፈለገው ወቅት ውጤት እያስመዘገበ ባለመሆኑ በቅንጅት መሥራት የሚችሉበት አዋጅ ፀድቆ ወደ ተግባር መግባቱን ገልፀዋል።
በሁሉም አካባቢ ያሉ የሲቪክ ማህረሰብ ድርጅቶች አገልግሎት የሚሰጧቸው የማህብረሰቡ አካላት እንዲለወጡ ፣በአካባቢው የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ጠንክረው በትብብር መሥራት እንዳለባቸውም አቶ ዳንኤል አሳስበዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ አካላትም በመድረኩ የተላለፉና በጋራ የተስማሙባቸው ሐሳቦችን ወደ ተግባር ለመቀየር እንደሚሠሩ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የሲቭክ ማህብረሰብ ድርጅቶች ሥራቸው በአግባቡ ተመዝኖ የሚመሩበት አሰራር መዘርጋት ስኬታማነቱ የተረጋገጠ እንዲሆን ያደርጋል ያሉት በመድረኩ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሲቭክ ማህብረሰብ ድርጅቶች ዳይሬክተር ማሞ ሞልሶ ናቸው።
ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
ማረሚያ ቤቶች ከማረምና ማነፅ ሥራዎች በተጨማሪ የልማት ሥራዎችን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ገለፀ
የሀገራችንን ሠላምና ልማት ለማስቀጠል የበጎ ፈቃድ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ገለፀ
ተመራቂ ተማሪዎች በሰለጠኑበት የሙያ መስክ ያላቸዉን እዉቀትና ክህሎት ተጠቅመዉ ዘመኑን የሚመጥን ስራ በመስራትና ተወዳዳሪ በመሆን ሀገራዊ ሀላፊነታቸዉን መወጣት እንዳለባቸዉ ተገለፀ