በበጎ ተግባራት የተሰማሩ ወጣቶች ለበርካታ አካል ጉዳተኞች ተስፋ መለምለም ምክንያት መሆናቸውን በከምባታ ዞን የሀደሮ ከተማ አስተዳደር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ
የ”አማኑኤል አካል ጉዳተኞች ማህበር” ሶስተኛ ቅርንጫፉን በሀደሮ ከተማ አስተዳደር በመክፈት ለብዙ አካል ጉዳተኞች ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ ተመላክቷል።
“አካል ጉዳተኝነት አለመቻል አይደለም” በሚል መፈክሩ ይታወቃል፣ በከምባታ ዞን በሀደሮ ከተማ ተወልዶ ያደገው የ”አማኑኤል አካል ጉዳተኞች ማህበር” መስራች ወጣት መለስ እዮብ።
በልጅነቱ ባጋጠመው የልጅነት ልምሻ ህመም ምክንያት በደረሰበት የአካል ጉዳት ለሁለት ዓመታት ክራንች በማጣት ብዙ እንደተንገላታ ተናግሯል።
በወላይታ ሶዶ ክርስትያን ሆስፒታል ነፃ ህክምና እንደተደረገለት የሚናገረው ወጣቱ፤ ከዚያ መነሻ ከ12 ዓመት በፊት በወላይታ ሶዶ “አማኑኤል አካል ጉዳተኞች ማህበር”ን በማቋቋም ድጋፍ ለማድረግ ወደ ስራ እንደገባ በመግለጽ የዊልቸር፣ የክራንች፣ የክራንች ፕላስቲክ ጎማ እና ህክምና ለሚያስፈልጋቸው አቅም ላጡ አካል ጉዳተኞች በነጻ ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግሯል።
ከዚህ ቀደም በወላይታ ሶዶ እና በሐዋሳ ከተሞች ማህበሩን በማስፋፋት እየሰራ እንደሆነ የገለጸው ወጣት መለስ፤ ወደ ትውልድ ቀዬው በመመለስ በሀደሮ ከተማ ሶስተኛ ቅርንጫፉን በመክፈት ለአካል ጉዳተኞች ድጋፍ ማድረግ መቀጠሉን አስረድቷል።
በተነሳሽነት በሚያደርገው ድጋፍ መንግስታዊና መንግታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሌሎችም ለአካል ጉዳተኞች በሚደረግ ድጋፍ የበኩላቸውን በማድረግ አጋርነታቸውን እንዲያሳዩም ጠይቋል።
ወጣት ብልጥነሽ ብርሃኑ ለበርካታ ዓመታት እግሯ ላይ በደረሰ ጉዳት ምክንያት በህመም ስትሰቃይ መቆየቷን በመግለጽ፤ በማህበሩ በተደረገላት ድጋፍ በወላይታ ሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል ነጻ ህክምና ማግኘት መቻሏን ተናግራለች።
ለሰባት አመት ልጃቸው የተደረገው የዊልቸር ድጋፍ ለልጃቸው ጤና መጠበቅ በብዙ እንዳገዛቸው የነገሩን ሌላው የድጋፉ ተጠቃሚ አቶ ዮሐንስ ናቸው።
በከምባታ ዞን የሀደሮ ከተማ አስተዳደር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አልማዝ ያዕቆብ፤ በበጎ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ለበርካታ አካል ጉዳተኞች ተስፋ መለምለም ምክንያት መሆናቸውን ተናግረዋል።
የአማኑኤል አካል ጉዳተኞች ማህበር ከእነዚህም አንዱ እንደሆነ በመግለጽ አካል ጉዳተኝነት አለመቻል አለመሆኑን በተግባር ያሳየ እንደሆነም ተናግረዋል።
እንደ ጽህፈት ቤት ለማህበሩ እውቅና ከመስጠት ጀምሮ በሚያስፈልገው ሁሉ ከጎኑ ነን ያሉት ኃላፊዋ፤ ለዚህ በጎ ተግባር በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪም ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በገንዘብና በአይነት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፡ ኤደን ተረፈ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የባስኬቶ ዞን ላስካ ከተማ አስተዳደር ህዝብ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤ ተካሂዷል
የባህር በር የሌላቸው ታዳጊ ሀገራት በዓለም የኢኮኖሚ ሥርዓት ላይ ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ እያደረጋቸው ይገኛል
በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት ለፍርድ ቤቱ ከቀረቡ መዝገቦች 573ቱ ውሳኔ ማግኘታቸው ተገለጸ