የባስኬቶ ዞን ላስካ ከተማ አስተዳደር ህዝብ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤ ተካሂዷል
ጉባኤው በምክር ቤቱና በአስተዳደር ምክር ቤቱ የተከናወኑ የሥራ ሪፖርቶችን፣ በጀትና ልዩ ልዩ ሹመቶችን በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።
የባስኬቶ ላስካ ከተማ አስተዳደር ህዝብ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ወይንሸት ታደለ፤ በታችኛው ምክር ቤት በየወቅቱ ጉባኤ በማድረግ ከመንግስት የሚወርዱ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ በመወሠን ህዝባዊ መሠረት ማስያዝና ተፈፃሚነታቸው ላይ የሚስተዋሉ ውስንነቶችና ጥሰቶች እንዲታረሙ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት የጋራ ርብርብ የሚሻ መሆኑን በመክፈቻ ንግግራቸው ገልጸዋል።
ያለፈውን ቃለ ጉባኤ በሙሉ ድምፅ በማፅደቅ መርሀ ግብሩን የጀመረው የምክር ቤቱ ውሎ በህዝብ ምክር ቤቱ በበጀት አመቱ የተከናወኑ ተግባራትና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድን አዳምጦ ሐሳብ አስተያየት ሰጥቶበታል።
ዋና አፈ ጉባኤዋ ወ/ሮ ወይንሸት ለተነሱ ርዕሰ ጉዳዮች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተው የቀረበው ሪፖርትና ዕቅድም በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።
የላስካ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር አንለይ ወንድፍራው፤ የአስተዳደር ምክር ቤቱን የ2017 በጀት ዓመት የሥራ ክንውንና የ2018 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ ዝርዝር ሪፖርት ለአባላቱ አቅርበዋል።
የምክር ቤቱ አባላትም ከቀረበው ሪፖርት በመነሳት በከተማው እየጨመረ የመጣውን የሥራ ፈላጊ ወጣት ቁጥር ለመቀነስ ለሥራ ፈጠራ ብድርና ቁጠባን ማመቻቸትና የህብረተሠቡን የመልማት ጥያቄ መሠረት ያደረገ የመሠረተ ልማት ተደራሽነት ትኩረት ይሻል ብለዋል።
በከተማው ማስፋፊያ ቀበሌያት የመሬት ሽንሸና ላይ የሚስተዋሉ የሙስና አዝማሚያዎች መኖራቸውን የጠቆሙት የምክር ቤቱ አባላት፤ ችግሩን በአፋጣኝ መርምሮ እልባት መስጠት ይገባል ነው ያሉት።
የላስካ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ያዕቆብ አሻግሬና ዋና ከንቲባው ኢንጂነር አንለይ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት፣ የሴት አደረጃጀቶችን ማጠናከርና የህጻናት ፍልሰትን መቆጣጠር፣ ከጤናው ረገድ የወባ በሽታ መሥፋፋት፣ የመድሀኒት ዋጋ ንረት ዙሪያም ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
የከተሞች ውበትና ጽዳትን ማስጠበቅና የኮሪደር ልማትን ማፋጠን ትኩረት ይሻል ያሉት አባላቱ፤ ህገ ወጥ የመሬት ይዞታዎችን መከላከልና የልማት ተነሺ የህብረተሰብ ክፍሎችን የተመለከቱ ጥያቄዎችንም አቅርበዋል።
በከተማው የሚመነጨውን የገቢ አቅም አሟጦ መሠብሰብ በራስ አቅም የመልማት ጥያቄን መመለሥ ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ከንቲባው ኢንጂነር አንለይ አፅኖት ሰጥተውበታል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሟሟቀ የመጣውን የባስኬት ቡና እግር ኳስ ክለብ እንቅስቃሴን ከየትኛውም ጫና በማላቀቅ ህዝባዊ መሠረቱን ይበልጥ ለማጥበቅ በልዩ ትኩረት ለመሥራት እቅድ መያዙ ተመላክቷል።
የምክር ቤቱ አባላት በሰፊው የተወያዩበትን የአስተዳደር ምክር ቤት ክንውን ሪፖርትና ጠቋሚ ዕቅድ በሙሉ ድምፅ አፅድቀዋል።
የላስካ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አፈጻጸም ሪፖርትና ጠቋሚ ዕቅድ በፍርድ ቤቱ ፕሬዝደንት ወ/ሮ ሙሉነሽ አመኑ ቀርቦ ምክር ቤቱ ተወያይቶበት በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።
የላስካ ከተማ አስተዳደር ህዝብ ምክር ቤት የ2018 በጀትን 186 ሚሊዮን 49 ሺህ 6 መቶ 97 ብር እንዲሁም ልዩ ልዩ ሹመቶችን መርምሮ በማፅደቅ ተጠናቋል።
ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን
More Stories
በበጎ ተግባራት የተሰማሩ ወጣቶች ለበርካታ አካል ጉዳተኞች ተስፋ መለምለም ምክንያት መሆናቸውን በከምባታ ዞን የሀደሮ ከተማ አስተዳደር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ
የባህር በር የሌላቸው ታዳጊ ሀገራት በዓለም የኢኮኖሚ ሥርዓት ላይ ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ እያደረጋቸው ይገኛል
በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት ለፍርድ ቤቱ ከቀረቡ መዝገቦች 573ቱ ውሳኔ ማግኘታቸው ተገለጸ