ለዜጎች ሰላምና ለሀገር ዕድገት የጸጥታዉ ዘርፍ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ

ለዜጎች ሰላምና ለሀገር ዕድገት የጸጥታዉ ዘርፍ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 30/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለዜጎች ሰላምና ለሀገር ዕድገት የጸጥታዉ ዘርፍ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ ተናገሩ።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም እና በ2018 መሪ ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቦንጋ ከተማ ውይይት እያካሔደ ነው።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ ለዜጎች ሰላም፣ ልማትና ለሀገር ደህንነት ጸጥታ ያለው ድርሻ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በዞኑ የጸጥታ ስጋት እንዳይፈጠር ከባለድሻ አካላት ጋር በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን ያነሱት አቶ እንዳሻው ይህ መልካም ተሞክሮ ዘላቂነት እንዲኖረው መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በተጠናቀቀው በጀት አመት ብቻ ከ116 ቶን በላይ ቡና በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር ተይዞ ለመንግስት ገቢ መደረጉን ያስታወሱት ዋና አስተዳዳሪው ይህ ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።

መሰረታዊ በሆኑ የግብርና ምርቶች፣ በነዳጅ፣ በጦር መሳሪያና ሌሎችም ዘርፎች የሚከናወኑ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን በቅንጅት መቆጣጠር የሁሉም አካላት ግዴታ ሊሆን እንደሚገባም ዋና አስተዳዳሪዉ አሳስበዋል።

በዞኑ ሰላምን በማጽናት ልማትና ዴሞክራሲ እንዲረጋገጥ ፖሊስ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ያሉት የካፋ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኢንፐክተር አጥናፉ አባተ፥ በትራፊክ አደጋ በዜጎችና ንብረት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለወንጀል መከላከል ተግባር መሳካት የህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ የላቀ ድርሻ እንዳለው ጠቁመዉ በዚህም ሥራ አንጻራዊ ለውጥ እየተመዝገበ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በዞኑ ከ40 በላይ የማህበረሰብ አቀፍ የወንጀል መከላከያ ጣቢያዎችን በማስገንባት በቅንጅት እየተሰራ ነው ያሉት ኢንስፔክተር አጥናፉ፥ ከ250 በላይ የጦር መሳሪያና በርካታ ጥይቶችን በክትትል መያዣቸውን ነው የተናገሩት።

የሀገር ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በሆነው ቡና ላይ የሚደረገው ህገ-ወጥ ግብይትና ዝውውር ላይ በቂ ቁጥጥር አለመኖሩን ገልጸዉ ሁሉም መዋቅሮች በትኩረት መስራ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ድንበር ተሻጋሪ የወንጀል ተግባራን ከመከላከልና የችግሩ ተዋናይና ፈጻሚ አካላትን ለህግ ከማቅረብ አንጻር አበረታች እንቅስቃሴዎች መኖራቸውንም አንስተዋል።

ዘጋቢ፡ በአሳምነው አትርሳው – ከቦንጋ ጣቢያችን