በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት ለፍርድ ቤቱ ከቀረቡ መዝገቦች 573ቱ ውሳኔ ማግኘታቸው ተገለጸ

በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት ለፍርድ ቤቱ ከቀረቡ መዝገቦች 573ቱ ውሳኔ ማግኘታቸው ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 30/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ2017 በጀት ዓመት ለፍርድ ቤቱ ከቀረቡ 578 መዝገቦች ውስጥ 573ቱ ውሳኔ ማግኘታቸውን አስታወቀ፡፡

በፍርድ ቤቱ በተሰጣቸው ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት መደሰታቸውን ተገልጋዮች ገልፀዋል፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሙከረም ኑረዲን እንዳስታወቁት በልዩ ወረዳው ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ መዝገቦች የቆይታ ጊዜን በማሳጠር ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት ለመስጠት በተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል።

የመዝገብ ክምችትና የቆይታ ጊዜን የመቀነስ እንዲሁም ጥራቱን የጠበቀ ውሳኔ ሥራ ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራቱን የገለፁት ፕሬዝዳንቱ፥ በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት ለፍርድ ቤቱ ከቀረቡ 578 መዝገቦች ውስጥ 573ቱ ውሳኔ ማግኘታቸውን ገልፀዋል ።

ለክስ እየቀረቡ ያሉ መዝገቦች ቁጥር ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር እየቀነሰ መምጣቱን የገለፁት አቶ ሙከረም አፈፃፀሙ ሊሻሻል የቻለውም ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት የሚመጡ መዝገቦች በማኅበራዊ ፍርድ ቤት እየታዩ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

መዝገቦችን በይግባኝና በሰበር የማጽናት አቅም እያደገ መምጣቱን ገልጸው በሕግ በተፈቀዱ ጉዳዮች አማራጭ የሙግት መፍቻ በማመቻቸትና ማመልከቻ ተኪ ቅጾችን በማዘጋጀት በጊዜና በጉልበት ላይ የሚደርሰውን ጫና ለማስቀረት እየተሠራ መቆየቱን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ከሚሰጠው የዳኝነት አገልግሎት በተጨማሪ 22 ቀለል ያሉ የወንጀልና የፍታብሔር መዝገቦች በሽምግልና ድርድር ውሳኔ ማግኘታቸውን ያስታወቁት አቶ ሙከረም ይህም የፍርድ ቤቶችን ጫና ከመቀነሱም ባሻገር ይባክን የነበረውን ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ ለመቆጠብ ማስቻሉን ተናግረዋል ፡፡

የአገልግሎት አሰጣጥ ተደራሽነትን ለማሳደግና የማኅበረሰቡን ወጪና እንግልት ለመቀነስ በወሸርቤ ከተማና በውጥኝ ክላስተር በሚገኙ ተዘዋዋሪ ችሎቶች 21 መዝገቦች ታይተው ውሳኔ ማግኘታቸውንም አብራርተዋል ፡፡

ከዳኝነት አገልግሎት ጨምሮ በፍታብሔርና በሌሎችም የህግ አገልግሎቶች ከ1 ሚልየን 700 ሺህ ብር በላይ ለመንግስት ገቢ መደረጉን ተናግረው ፍርድ ቤት ቀርበው መከራከር ለማይችሉና የአቅም ውስንነት ላለባቸው ለ97 የህብረተሰብ ክፍሎች ነፃ የህግ፣ የጥብቅናና የምክር አገልግሎት መሰጠቱንም አስታውቀዋል ፡፡

በ2018 በጀት አመት ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር የመዝገብ ክምችትና የቆይታ ጊዜን የመቀነስ እንዲሁም ተቋማዊ አቅም በቴክኖሎጂና በሰው ሀይል የማጠናከር ስራ እንደሚሰራም ገልፀዋል ፡፡

አቶ አህመድ ጦሃ እና አቡበክር ኢማሙ በፍርድ ቤቱ አግኝተን ካነጋገርናቸው ተገልጋዮች መካከል ይገኙበታል፡፡

በተሰጣቸው ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት መደሰታቸውንና አገልግሎቱ በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልፀዋል ፡፡

ዘጋቢ፡ ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን