የጉራጌ ህዝብ የታታሪነት ልምዱን በፀረ ሙስናና በብልሹ አሰራር ትግሉ ላይ መድገም አለበት ሲል የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ገለፀ

የጉራጌ ህዝብ የታታሪነት ልምዱን በፀረ ሙስናና በብልሹ አሰራር ትግሉ ላይ መድገም አለበት ሲል የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ገለፀ

የ2017 በጀት አመት የጉራጌ ዞን ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ጥምረት ጉባኤ በወልቂጤ ከተማ ተካሒዷል።

የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ታየች ሞላ፤ የጉራጌ ህዝብ በስራ ወዳድነት፣ በታታሪነትና በመረዳዳት ለሌላው ተምሳሌት እንደሆነ ገልፀው ይህንን ልምዱን በፀረ-ሙስናና ብልሹ አሰራር ትግሉ መደገም አለበት ብለዋል።

በክልሉ ጠንካራ የሙስና ወንጀሎች ለመከላከል በቁርጠኝነት ከሚሰሩ መዋቅሮች መካከል የጉራጌ ዞን ግንባር ቀደም ነው ያሉት ኮሚሽነር ታየች፤ ይህንን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ሙስናን የሚጸየፍ ትውልድ መፍጠር ከሁሉም ቅድሚያ የሚሰጠው እንደሆነ በመጠቆም ለዚህም የሐይማኖትና ትምህርት ተቋማት ጉልህ ድርሻ አላቸው ብለዋል።

ወቅቱን የጠበቀ የኦዲት ክትትል ከማድረግ ባሻገር በኦዲት ግኝት ላይ ተጨባጭ እርምጃ በመውሰድ ጠንካራ የንብረትና የፋይናንስ የኦዲት ስርአት መዘርጋት ያስፈልጋል ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው።

የመልካም አስተዳደር ስራ ውስንነት ለሌብነትና ብልሹ አሰራር ሊጋብዝ ስለሚችል አገልግሎት በማዘመን ሙስናን መከላከል እንደሚገባ አቶ ላጫ ተናግረዋል።

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የጥምረቱ ስራ አስፈፃሚ አቶ አበራ ወንድሙ በጸረ-ሙስና ዙሪያ ትምህርትና ስልጠና በመስጠት የህብርተሰቡን ግንዛቤ ከፍ ከማድረግ በተጨማሪ በየደረጃው ሙስናና ብልሹ አሰራር እንዳይፈፀም የመከላከልና ከዚህም አልፎ ሲገኝ ህጉ በሚፈቅደው መሠረት ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ በማስወሰን የህዝብና የመንግስት ሀብት ተመላሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች መሠራታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ህዝባችን የትግሉ ባለቤት በማድረግ በተንቀሳቀስነው ልክ አበረታችና ለቀጣይ ስራዎች ከፍተኛ መነሳሳት ያገኘንባቸው ውጤቶች ተመዝግበዋል ያሉት አቶ አበራ፤ የሙስናና ብልሹ አሰራር ትግል በማጠናከር የህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደደር ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንቅሳቀስ ይጠበቃል ብለዋል አቶ አበራ፡፡

የዞኑ አስተዳደር የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ጥምረት ሴክሬታሪ አቶ ጀማል አህመድ በበኩላቸው፤ በ2017 በጀት አመት ጠንካራ የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስናን የመከላከል እና አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ሲደረግ እንደነበር ገልፀዋል።

አቶ ጀማል አክለውም፤ በዞኑ ውስጥ የአፈር ማዳበሪያ መጋዘኖች ኦዲት፣ ህገወጥ የቤት ዝውውር የአገልግሎት ግዢ ጥራት ቁጥጥር፣ በገጠርና ከተማ የመሬት ወረራ እንዲሁም የትምህርት ንብረት አስተዳደር በአስቸኳይ ሙስና መከላከል ስራዎች መሰራታቸው ገልፀዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ሙስና ከመናገር ባሻገር ለመከላከል ንፁህ ህሊናና እጅ ይዞ መገኘት እንደሚጠይቅ በመግለፅ ለዚህም በትውልድ ላይ በመስራት ሙስና የሚጸየፍ ህዝብ መገንባት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሌብነት በየትኛውም ሃይማኖት የማይፈቀድና እንደ ባህል አፀያፊ ተግባር በመሆኑ አሰራሮችን በመፈተሽ ተጠያቂነት ማስፈን እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

የሙስና ወንጀል በተናጠል ግለሰቦችን ብቻ የሚያጠቃ ባለመሆኑ ብዙሃኑ ማህበረሰብና መንግስት ተግባሩን ለማክሰም ተባብሮ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።

ዘጋቢ፡ ፍስሃ ክፍሌ – ከወልቂጤ ጣቢያችን