እድሮች በበጎ ተግባርና በሰብአዊ ጉዳዮች ላይ የተጠናከረ ስራ ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ

እድሮች በበጎ ተግባርና በሰብአዊ ጉዳዮች ላይ የተጠናከረ ስራ ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 29/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) እድሮች በበጎ ተግባርና በሰብአዊ ጉዳዮች ላይ የተጠናከረ ስራ ሊሰሩ እንደሚገባ የአርባምንጭ ከተማ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ጽ/ቤት ገለጸ፡፡

ባለፈው በጀት አመት ኤስ.ኦ.ኤስ ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅትና እድሮች ጋር በመተባበር 180 ለሚሆኑ ሴቶች ከ1 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ መቻሉ ተጠቁሟል።

ከ300 በላይ ለሚሆኑ ህጻናት ደግሞ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ምድረጉም ተመልክቷል።

ወ/ሮ ሀሙሴ ከተማና መስከረም ቡሳ የአርባምንጭ ከተማ የጫሞ ቀጠና ነዋሪዎች ሲሆኑ የጅንካ በር እድርና SOS ድርጅት በጋራ በመሆን ለልጆቻቸው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍና የቤት እድሳት ስላደረጉላቸው ደስተኞች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሌላኛዋ እስተያየት ሰጪ መሠረት ደሳለኝ የበጎ ተግባሩ ተጠቃሚ መሆኗን ገልጻ በተለይ ለልጇቿ የትምሀርት ቁሳቁስና የደንብ ልብስ በማሟላት እንዳገዟቸውና በተለይ መኖርያ ቤታቸው በጥሩ ሁኔታ መታደሱ በዝናብ ወቅት የሚቸገሩትን የሚያስቀርላቸው እንደሆነ ገልጻለች።

የበጎ ተግባሩ ተጠቃሚዎች አክለውም የጅንካ በር እድርና የSOS ድርጅት ስላደረጉላቸው መልካም ተግባር አመስግነዋል።

በአርባምንጭ ከተማ የጅንካ በር እድር ስራ አሰኪያጅ አቶ አለማየሁ ደነቀ የሞተን ከመቅበርና ማስተዛዘኛ ከማድረግ ባለፈ በሰብአዊ ተግባራት ላይ ከSOS ድርጅት ጋር በመተባበር አቅመ ደካሞችን በገንዘብና በቁሳቁስ የመደገፍና ለታዳጊ ህጻናት የትምህርት ቁሳቁስና አልባሳት የማሟላት ስራ እየሰራን ነው ብለዋል።

የSOS የህጻናት መንደር የቤተሰብ ማጠናከርያ ፕሮጀክት ኦፊሰር አቶ ጴጥሮስ ኦይዳ ድርጅቱ በኢትዮጵያ በተለያዩ አከባቢዎች ከ 50 አመታት በላይ እየሰራ መቆየቱን ጠቅሰው ህጻናት ደህንነታቸው ተጠብቆ ከቤተሰብ ጋር እንዲያድጉ የሚደግፍ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

እስካሁን ፕሮጀክቱ በአርባምንጭ ከተማ የባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በጫሞና በእድገት በር ቀጠና ለትምህርት ቤቶች ለታዳጊ ህጻናትና ለአቅመ ደካሞች በሁለቱ ቀጠና የሚገኙ እድሮችን በመጠቀም ለበርካቶች ተደራሽ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

የአርባምንጭ ከተማ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ የምስራች ማሞ ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ከእድሮች ጋር በመሆን በዋናነት የቤተሰብን አቅም መገንባት ላይ እንደሚሰራ ገልጸዋል ።

እስካሁንም 180 ለሚሆኑ ሴቶች ከ 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስራዎች ማሳተፉንና ከ300 በላይ ለሚሆኑ ህጻናት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ሌሎች እድሮችም ተሞክሮ በመውሰድ ከለቅሶ ባሻገር በበጎ ተግባርና በሰብአዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የተጠናከረ ስራ ሊሰሩ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ዘጋቢ ፡ ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን