አምራች ኢንደስትሪዎች ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች በጥራት እንዲያመርቱ አቅም ለማጎልበት የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የኢንደስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ

አምራች ኢንደስትሪዎች ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች በጥራት እንዲያመርቱ አቅም ለማጎልበት የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የኢንደስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ

በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ አስተዳደር በማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ መካከለኛ አና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የስራ እንቅስቃሴ አስመልክቶ የመስክ ምልከታ ተካሂዷል።

የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የኢንደስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ናትናኤል ሚሊዮን እንዳሉት፤ ጉብኝቱ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ያሉ ችግሮችን ከመፍታት ባሻገር አምራቾችን በማጠናከር የማምረት አቅማቸውን ለማጎልበት ያለመ ነው።

በወልቂጤ በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ኢንደስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሚደገፉ 24 ምርትን የሚያቀነባብሩ አምራች ኢንደስትሪዎች መኖራቸውን ያወሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ እነዚህ ኢንደስትሪዎች የስራ እድል ከመፍጠር ባሻገር ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶች እያመረቱ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ኮርፖሬሽኑ አምራች ኢንደስትሪዎች ያሉባቸውን ውስንነቶች ከመቅረፍ በተጨማሪ ለውጭ ኤክስፖርት መደረግ የሚችል ጥራት ያለው ምርት ማምረት እንዲችሉ ለማድረግ የጀመረውን ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ናትናኤል ሚሊዮን ገልጸዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው የሮሆቦት ባልትና እና ሌሎችም በራሳቸው ጥረት ወደ ውጭ መላክ የሚችሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶች እያመረቱ መሆኑን በምልከታው ማረጋገጣቸውን ጠቁመው፤ ይህም ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች በማስቀረት በራስ አቅም ማምረት እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

ማህበራቱ ይህንኑ ተግባር ይበልጥ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረው፤ በቀጣይም የዞኑ አስተዳደር ማህበራቱ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግም ገልፀዋል አቶ ላጫ።

የጉራጌ ዞን ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙራድ ያሲን እንዳሉት፤ በዞኑ ከ8 ሺህ በላይ ኢንተርፕራይዞች በገጠርና በከተማ በአገልግሎት፣ በኢንደስትሪና በግብርና ዘርፍ ተሰማርተው እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

ኢንተርፕራይዞቹ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ዜጎች የስራ እድል እንዲፈጥሩ መንግስት ለአምራቹ ዘርፍ ትኩረት በመስጠት የመስሪያ፣ የመሸጫ ቦታ እና ሌሎችም ድጋፎች እያደረገ መሆኑና በቀጣይም ተጨማሪ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ለማፍራት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

በምልከታው ኢንተርፕራይዞች በራሳቸው እሴት ጨምረው ትላልቅ ማሽነሪዎች በመጠገን፣ የባልትና ውጤቶች እስከ ውጭ ድረስ መላክ እንደሚችሉ ተመልክተናል ያሉ ሲሆን እነዚህን መደገፍ፣ ማብቃትና ሌሎችም ወደዚህ ዘርፍ እንዲቀላቀሉ ለማድረግ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር ለኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ የሆነውን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለማጠናከረ በተሰራው ስራ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

በተለይም የሮሆቦት የባልትና ውጤቶች አምራች ማህበር ለ80 ስራ አጥ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩንና ማህበሩ ወደ ኢንቨስትመንት ለመሸጋገር ያቀረበው ጥያቄ ውጤታማ እንዲሆን ድጋፍ ይደረጋል ነው ያሉት።

የተጎበኙ የአምራች ኢንደስትሪዎች ባለድርሻዎች መንግስት ባደረገላቸው ድጋፍ በማህበር ተደራጅተው ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግረው፤ አሁን ላይ በስራቸው ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም ለበርካታ ስራ አጥ ዜጎች የስራ አድል ከመፍጠር ጀምሮ ለውጭ ኤክስፖርት መደረግ የሚችሉ ምርቶች እያመረቱ ስለመሆኑ ገልጸው፤ መንግስት የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አመላክተዋል።

በእለቱ በወልቂጤ እና ጉብሬ ክፍለ ከተማ ያሉ የሮሆቦትና የእልፉ ባልትና እንዲሁም በቴራዞና በሌሎች በፋብሪካ ምርቶች ተግባር የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች መመልከት ተችሏል።

በመጨረሻም በመስክ ምልከታው የተሳተፉ አካላት የችግኝ ተከላ ፕሮግራም አካሂደዋል።

ዘጋቢ፡ አማን ቢካ – ከወልቂጤ ጣቢያችን