በቀቤና ልዩ ወረዳ በግብርና ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸው ተገለፀ

በቀቤና ልዩ ወረዳ በግብርና ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸው ተገለፀ

በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት በአደይ ፕሮግራም ድጋፍ በልዩ ወረዳው የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች የበቆሎ ሰብል ማሳ የመስክ ምልከታ ተካሂዷል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ አቡበከር ዱላ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ በልዩ ወረዳው ወጣቶችን በማደራጀት በስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወነ ነው።

በዚህም በተለይም አሁን ላይ በሰብል ልማት የተሰማሩ ወጣቶች በ26 ሄክታር መሬት ላይ እያለሙት የሚገኘው የበቆሎ ሰብል ማሳ ውጤታማነት ተስፋ ሰጪ መሆኑን አመላክተዋል።

ይህም ለሌሎች ወጣቶችና አርሶ አደሮች ተሞክሮ እንደሚሆን በመጥቀስ ሌሎች ወጣቶች ተሞክሮውን በመተግበር፣ ምርታማነትን በማላቅና የአካባቢው ጸጋዎችን በመጠቀም ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

በልዩ ወረዳውና በሌሎችም ባለድርሻ አካላት በኩል በአደይ ፕሮግራም ለታቀፉ ኢንተርፕራይዞች ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝና ድጋፉ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ሙዴ ሙዘሚል፤ በርካታ ስራ አጥ ወጣቶች ወደ ስራ እንዲገቡ ሰፊ ጥረት መደረጉንና ክህሎት መር ስልጠና በመስጠት በተለያዩ የስራ ዘርፎች መሰማራታቸውን ተናግረዋል።

በልዩ ወረዳው የተደራጁ ወጣቶች ውጤታማ እንዲሆኑ የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝና በተለይም በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶች መኖራቸውን በማንሳት የአደይ ፕሮግራም የስልጠና፣ የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ድጋፍ እንዳደረገላቸው በመግለፅ ፕሮግራሙ ለልዩ ወረዳው ኢንተርፕራይዞች እያደረገ ያለውን ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ የገጠር ወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ ዘርፍ ባለሙያና በቢሮው የአደይ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ደምስ ስርበሞ በበኩላቸው፤ ፕሮግራሙ በክልሉ በ7 ዞኖችና በ1 ልዩ ወረዳ እየተተገበረ ይገኛል ነው ያሉት።

ፕሮግራሙ በዘርፉ ለተለዩ ስራ አጥ ወጣቶች የክህሎት ስልጠናና ግብዓትን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎች እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ፕሮግራሙ በቀቤና ልዩ ወረዳ በኢንተርፕራይዝ ዘርፍ ለተደራጁ ወጣቶች እያከናወነ የሚገኘው የስልጠናና የግብዓት ድጋፍ ማሳያ መሆኑን ገልጸው፤ በልዩ ወረዳው ድጋፍ የተደረገላቸው በሰብል ልማት የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ምርታማነታቸውን ለማሳደግና ለመለወጥ እያደረጉት ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን ተከትሎ አድናቆታቸውን ቸረዋል።

በልዩ ወረዳው ለወጣቶቹ እየተደረገ ያለውን የመሬትና መሠል ድጋፎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን በመጥቀስ ፕሮግራሙ እያደረገ ያለው ድጋፍ በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በልዩ ወረዳው የተጎበኘው የአሴም ለሌንሳም ኢንተርፕራይዝ አባላት መካከል በሰጡት አስተያየት ተደራጅተው ወደ ስራ በመሰማራታቸው ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸው የአደይ ፕሮግራም የክህሎት ስልጠና፣ የበቆሎ ምርጥ ዘርና የማዳበሪያ ድጋፍ እንዳደረገላቸው ተናግረዋል።

በቀጣይ የተሻለ ምርት ለማግኘት ጠንክረው እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በመስክ ምልከታው ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳን ጨምሮ የልዩ ወረዳው አመራሮች እና የቢሮው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፡ መሀመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን