የሣውላ ከተማ ምክር ቤት የከተማውን የ2018 ዕቅድ ማስፈፀሚያ በጀት ከ594 ሚሊዮን በላይ ብር በሙሉ ድምጽ አጸደቀ
ምክር ቤቱ ባካሄደው 4ኛ ዙር መርሃ ግብር 12ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤው ልዩ ልዩ ሪፖርቶችንም አዳምጦ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።
የሣውላ ከተማ ህዝብ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ዘሪሁን ትርንጎ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ምክር ቤቱ ከፍተኛ የህዝብ ሥልጣን ባለቤት ሲሆን ተልዕኮውም በህዝብ የነቃ ተሳትፎ ለከተማው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ፋይዳ ያላቸውን ህጎችን በማውጣት አስፈፃሚውን የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ ነው።
ምክር ቤቱ ያለፈውን የምክር ቤት ጉባኤ ቃለ ጉባኤ መርምሮ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።
ምክትል አፈ ጉባኤዋ ወ/ሮ ማርታ አበራ፤ የ2017 በጀት ዓመት የሳውላ ከተማ ህዝብ ምክር ቤትን አፈፃፀም ሪፖርት አቅርበው በአባላቱ ሀሳብና አስተያየት ተሰጥቶበታል።
ከዚህ ቀደም በሪፖርት የተመላከቱ የኦዲት ግኝቶችን ማስመለስ ዙሪያ የታዩ ውስንነቶች፣ የቋሚ ኮሚቴዎች ለተቋማት የሚያደርጉት ድጋፍና ክትትል መጠናከር እንዲሁም ለቋሚ ኮሚቴዎች የተሠጡ ሥልጠናዎች በጠንካራ ጎን ተነስተዋል።
ሁሉም ምክር ቤቶች ወቅቱን ጠብቀው ጉባኤ ከማድረግ ረገድ የታዩ ጉድለቶች መታረም እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
በተነሱ ጥያቄዎች ላይ ምክትል አፈ ጉባኤዋ ወ/ሮ ማርታ ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በተለይ በከተማው ምክር ቤት የሚስተዋለው የቴክኖሎጂና የተለያዩ የመሥሪያ ቁሣቁሶች አለመሟላት በምክር ቤቱ ተግባር ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን በሰፊው ያብራሩ ሲሆን የቀረበው የምክር ቤቱ ሪፖርትም በአባላቱ በሙሉ ድምፅ ጸድቋል።
የሳውላ ከተማ ከንቲባ ዶ/ር ንጉሤ መኮንን፤ የአስተዳደር ምክር ቤቱን ሪፖርት አቅርበው በምክር ቤቱ አባላት ሀሳብና አስተያየት ተሰጥቶበት በሙሉ ድምፅ ጸድቋል።
ምክር ቤቱ በ4ኛ ዙር መርሃ ግብር 12ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤው የ2018 በጀት 594 ሚሊየን 550 ሺህ 379 ብር እንዲሆን የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።
የከተማው ፋይናንስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ እሴይ ሠራዊት፤ የበጀት ረቂቁን እና በጀቱ የሚውልባቸውን የልማት መስኮች በዝርዝር ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
በጀቱ በከተማዋ ለሚካሄዱ የዘላቂ ልማት ግቦችና ለአስተዳደራዊ ተግባራት እንደሚውል ባቀረቡት የበጀት ረቂቅ አመላክተዋል።
የበጀቱ ምንጭ ከመንግሥት ግምጃ ቤት፣ በከተማው ከሚሰበሰብ ገቢ፣ ከጤና ተቋም ገቢ፣ ከትምህርት ተቋማት ገቢ፣ ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ፣ ከመንግሥት ከሚሰጥ ድጎማና ሌሎች ምንጮች ስለመሆኑም አስረድተዋል።
በጀቱ ለድህነት ቅነሳ፣ ለመሠረተ ልማት ዝርጋታ እንዲሁም የነዋሪውን የልማት ተጠቃሚነት ለሚያረጋግጡ ተግባራት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ምክር ቤቱም የቀረበለትን የከተማውን የ2018 ዕቅድ ማስፈፀሚያ በጀትም በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን
More Stories
በመንግስትና ህብረተሰብ ትብብር በሚሰሩ ሥራዎች መሠረታዊ የልማት ጥያቄዎች እየተፈቱ መሆኑን በጉራጌ ዞን የአገና ከተማ አስተዳደር ገለጸ
በቀቤና ልዩ ወረዳ በግብርና ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸው ተገለፀ
በጌዴኦ ዞን የ2017 በጀት ዓመት በሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕይዝ ዘርፍ የተሻለ ውጤት የተመዘገበበት ዓመት መሆኑን የዞኑ ሥራና ክህሎት መምሪያ ገለጸ