በደቡብ ኦሞ እና በኣሪ ዞን ማህበረሰብ መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችን በማስወገድ በልማት እርስ በእርስ በማስተሳሰር ሰላምን ለማፅናት በአካባቢዉ የፖሊስ ፋዉንዴሽን ተቋቋመ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍሰሃ ጋረደዉ እንደገለፁት፤ ፖሊስ ከተሰጠዉ ህግ የማስከበር ስራ ጎን ለጎን ህዝቡ በሚያደርጋቸዉ ማንኛዉም ማህበራዊ ጉዳዮች ተሳትፎ ማድረግ ስላለበት በደቡብ ኦሞ ዞንና በኣሪ ዞን ማህበረሰብ መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችን በማስወገድ ሰላምን ለማፅናት በሁለቱ ማህበረሰቦች ይሁንታ በተቋቋመዉ የፖሊስ ፋዉንዴሽን የሚለማዉ የእርሻ ልማት የህዝቦችን የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥና ለወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥር በመሆኑ ሰላምን ለማፅናት በሚደተገዉ ስራ ማህበረሰቦቹ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የህግ አማካሪና የፖሊስ ፋዉንዴሽን የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አዳነ ገበዬሁ፤ ሰዉ ተኮር ስራ በመስራት ክልሉን የብልፅግና እና የሠላም ተምሳሌት ለማድረግ የፖሊስ አባሉ ከሰላም ማስከበር ስራዉ ጎን ለጎን እንደማንኛዉም ዜጋ የልማት ተጠቃሚ እንዲሆንና ማህበረሰቡ ሰላሙ ተጠብቆ የልማት ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ ነዉ ብለዋል፡፡
የኣሪ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ አብረሃም አታ በበኩላቸዉ፤ በአርሶ አደሩ እና በአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ዘንድ የሚፈጠሩ የከብት መዘራረፍና የሰዎች ሞትን በማስቀረት ማህበረሰቡን ወደ ልማት በማስገባት የስራ እድል ተፈጥሮላቸዉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን 200 ሄክታር መሬት እንደሚያለሙ ተናግረው፤ በቀጣይ አካባቢዉ የስጋት ቀጠና ከመሆን አልፎ ሀብት የሚገኝበት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
በኣሪ ዞን የደቡብ አሪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግዛዉ ኃይሌ፤ ፋዉንዴሽኑ ስራ ሲጀምር የሁለቱ ዞኖች ማህበረሰብ ከዘርፉ ተጠቃሚ የሚሆኑበት በመሆኑ የሳይት ርክክብ መደረጉን እንዲሁም በቀጣይ ካምፕ ሲሰራ ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጥበት በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸዉን ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ኦሞ ዞን ፖሊስ አዛዥ ረዳት ኢኒስፔክተር ጌትነት ካሳ፤ በሁለቱ ዞኖች የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለማስወገድ በተደጋጋሚ ሰላምን የማስፈን ስራዎች እየተሰሩ የቆዩ ቢሆንም ዘላቂ ሰላም ማምጣት እንዳልተቻለና አሁን ደግሞ ይህ የፖሊስ ፋውንዴሽን ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ከማድረጉ ባሻገር ዘላቂ ሰላምን ለማፅናት ወሳኝ ሚና ስላለው የሁለቱም ዞኖች የፖሊስ መዋቅር ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽኑ ጉን በመሆን በቅንጅት የወንጀል መከላከል ስራዉን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባና ማህበረሰቡም ፋዉንዴሽኑን በመደገፍ ችግር የሚፈጥሩ አካላትን ለህግ አሳልፈዉ መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በርክክቡ ወቅት ያገኘናቸዉ አርሶ አደሮች የፋዉንዴሽኑ መቋቋም የዘመናት የሰላም እጦት ችግራቸዉን የሚቀርፍ በመሆኑ አስፈላጊዉን ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡ በናወርቅ መንግስቱ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
የሚዛን አማን ከተማ ፖሊስ ጽ/ቤት በበጀት አመቱ ከማህበረሰቡ በመቀናጀት የከተማዋን ሠላምና ፀጥታ ለማስከበር ከፍተኛ ስራ መስራቱን ገለጸ
ጽዱ ከተማ ለመፍጠር የህብረተሰብ ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚገባ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ገለፀ
ፖሊስ ከመደበኛ ስራዉ ጎን ለጎን ከማህበረሰቡ ጋር በጋራ የሚያካሂደዉን የልማት ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ