ምክር ቤቱ ለ2018 በጀት ከ578 ሚሊዮን ብር በላይ ማጽደቁ ተገለጸ
የቡርጂ ዞን ምክር ቤት 5ኛ ዙር 3ኛ የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን በሶያማ ከተማ አካሂዷል።
ምክር ቤቱ በሁለት ቀናት ቆይታው የሴክተር መስሪያ ቤቶችን የ2017 በጀት ዓመት ሪፖርት አድምጦ እና በ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ መምከሩን የቡርጂ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወለቱ ዋዮ ለደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ይርጋጨፌ ሬዲዮ ጣቢያ አስታውቀዋል።
በበጀት ዓመቱ በመንገድ መሠረተ ልማት ዙሪያ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት የአዳዲስ የገጠር መንገዶች ከፈታና የማስፋፊያ ሥራዎች መከናወናቸውን የጠቆሙት አፈ ጉባኤዋ፤ የሶያማ ከተማን ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ለኢንቨስትመንት ሳቢ እንዲሆን በኮሪደር ልማት ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በሶያማ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የሚስተዋለው የግብአት አቅርቦት ውስንነት፣ የአዋር ክላስተር ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግርና ሌሎች ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆቸውን ዋና አፈ ጉባኤዋ አንስተዋል።
አክለውም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተመዘገቡ ስኬቶችን ማስቀጠልና የተለዩ ጉድለቶችን በማረም ለህብረተሰቡ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
ምክር ቤቱ ለሁለት ቀናት ባካሄደው ጉባኤ ለ2018 በጀት 5 መቶ 78 ሚሊዮን 8 መቶ ሺህ 7 መቶ 14 ብር ለጉባኤው ቀርቦ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።
በጉባኤው ማጠቃለያም ወ/ሮ ኤልሻዳይ ጴጥሮስን የሶያማ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት አድርጎ ሾሟል።
ዘጋቢ: አሀዱ አሸናፊ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
በሩብ ዓመቱ 3.7 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ወሰነች ቶማስ ገለጹ
የማር ምርት እጅግ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በጎምቦራ ወረዳ በንብ ማነብ ስራ የተሠማሩ አርሶአደሮች ተናገሩ
ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሰ የግብርና ልማት ላይ አደጋ እንዳያስከትል ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ተገለጸ