የደረጃ “ሐ”ግብር አሰባሰብ ስራ በሁሉም የታክስ ማዕከላት እየተከናወነ ቢሆንም የሲስተም ችግር መኖሩ በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እንቅፋት መፍጠሩ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 22/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሐምሌ 1 የጀመረው የደረጃ “ሐ “ግብር አሰባሰብ ስራ በሁሉም የታክስ ማዕከላት እየተከናወነ ቢሆንም ከቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ የሲስተም ችግር መኖሩ በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እንቅፋት መፍጠሩን የአርባምንጭ ከተማ ገቢዎች ጽ/ቤት ገለጸ፡፡
የአከራይ ተከራይ ግብር ግን 80 ከመቶ መጠናቀቁ ተመላክቷል።
አቶ አሀዱ ታመነ በአርባምንጭ ከተማ የቤሬ እድገት በር ቀበሌ የደረጃ “ሐ”ታክስ ከፋይ ሲሆኑ ግብር ቀድመው በመክፈላቸው የምስጋና ሰርተፍኬት እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።
ሌላኛው በነጭ ሳር ክፍለ ከተማ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋይ አቶ ናስር አወል የዘንድሮውን ግብር በዘመነ መልኩ በቴሌ ብር ቀድመው መክፈላቸውን ተናግረዋል።
ግብር መክፈል ለሀገር ልማትና እድገት አስዋጽኦ አለው የሚሉት አቶ አሀዱና አቶ ናስር ሁሉም ግብርን በመክፈል ረገድ ግንባር ቀደም መሆን አለበት ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
እንደ አስተያየት ሰጭዎቹ ገለጻ የሲስተም ችግር በግብር አከፋፈሉ ላይ የተወሰነ መስተጓጎል እንደፈጠረ ተናግረዋል።
የነጭ ሳር ታክስ ማዕከል ኃላፊ አቶ አሜሪካን አዲዮና የቤሬ እድገት በር ቀበሌ ታክስ ማዕከል ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ዳና ቀደም ብሎ ሰፊ የንቅናቄ ስራ በመሠራቱ ግብር ከፋዩ ከሐምሌ አንድ ጀምሮ በነቂስ በመውጣት የሚጠበቅበትን ግብር እየከፈለ ነው ብለዋል።
የግብር አከፋፈሉ በቴክኖሎጂ በመታገዝ በቴሌ ብር እየተከናወነ ቢሆንም የሲስተም ችግር ጎልቶ መታየት ለግብር አሰባሰቡ እንደ ማነቆ የሚነሳ ነው ብለዋል።
የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባና የገቢዎች ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ከንቲባ እንዳሉት በከተማው 14 ሺህ 553 የደረጃ “ሐ “ግብር ከፋዮች መኖራቸውን ጠቅሰው፥ የታክስ ስርአቱን ለማዘመን በተሰራው ስራ በ 2017 በጀት ዓመት ከ 9 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑ ግብር ከፋዮች በቴሌ ብር የሚከፍሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከሐምሌ አንድ ጀምሮ ግብር ከፋዩ በነቂስ ወጥቶ ግብሩን እየከፈለ ቢሆንም ከቴሌ ብር አከፋፈል ጋር ተያይዞ የሲስተም ችግር ጎልቶ መታየት፣ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ስም አለመዛወርና በተወካይ ስም መክፈል አለመቻልና መሠል ችግሮች የግብር አከፋፈሉ በፍጥነት እንዳይጠናቀቅ እንቅፋት እንደፈጠረ ገልጸዋል።
በከተማዋ ያሉ የታክስ ማዕከላት ሲስተም በማይጨናነቅበት በማለዳና እሰከ ምሽት ድረስ እየሰሩ መሆናቸውንና የ2017 ዓ.ም የአከራይ ተከራይ ግብር 80 ከመቶ መጠናቀቁን የሚገልጹት ወ/ሮ ሊዲያ፥ ግብር ከፋዮች የሚታየውን የሲስተም መጨናነቅ በትዕግስት በማለፍ በቀሪ ቀናት ግብራቸውን ከፍለው እንዲያጠናቅቁ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ ፡ ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
በዓልን ምክንያት በማድረግ የሚከሰት ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ገበያ የማረጋጋት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ
የንግዱ ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ መነጋገር ያስፈልጋል – አቶ አንተነህ ፍቃዱ
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ግንቦት 26/2017 ዓ.ም