የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን በማስፋፋት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን የቦንጋ ዩኒቨርስቲ ገለጸ

የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን በማስፋፋት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን የቦንጋ ዩኒቨርስቲ ገለጸ

ዩኒቨርሲቲው ከምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ የማህበራዊ ሳይንስ ምርምር ድርጅት (OSSREA)  ጋር በመተባበር  በካፋ ዞን ቢጣ ወረዳ ሸዳ ቀበሌ መርሃ ግብር ችግኝ ተከላ አካሂዷል፡፡

የካፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ደመላሽ ንጉሴ መርሃ ግብሩ በሀገር ደረጃ “በመትከል ማንሰራራት ” በሚል መርህ የተጀመረዉ ሁለተኛው ዙር  ችግኝ ተከላ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

ቡና የዞኑ ልዩ መገለጫ ነው ያሉት አቶ ደመላሽ ንጉሴ በቡና ልማት ላይ በተደረገው ርብርብ የማሳ ሽፋንን ከ200 ሺህ በላይ ማድረስ ተችሏል ብለዋል።

እየተተከሉ ያሉት ችግኞች የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባሻገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ፋይዳቸው የላቀ ነው ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲዉ የቡና ሳይንስ ተማሪና የኦስርያ ፕሮጀክት አማካሪ አቶ ወርቁ ዓለሙ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ከስፓኒሽ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት በተገኘ ድጋፍ ከምስራቅና ደቡብ አፍሪካ የማህበራዊ ሳይንስ ምርምር ድርጅት ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

 ዩኒቨርሲቲው ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውንና በምርምር የተረጋገጡ ችግኞችን በማዘጋጀት ለአካባቢው ማህበረሰብ እያከፋፈለ ነው ብለዋል ።

በተፈጥሮ ሐብት አያያዝና አጠቃቀም በአፍሪካ ዉስጥ ካሉት ስመ-ጥሩ ዩንቨርስቲዎች በ2030 (እኤአ) ግንባር ቀደም ለመሆን የሰነቀዉን ራዕይ እዉን ለማድረግ በዩኒቨርስቲዉ ቅጥር ግቢና ዉጪ በተለያዩ ወረዳዎች ለምርምርና ለማህበረሰብ አገልግሎት ሊውሉ የሚችሉትን ችግኞች በመትከል እየተንከባከበ ይገኛል ብለዋል፡፡

ማህበረሰቡ የተሻለ ኑሮ እንዲኖረው: በምርምር የተደገፈ አስተራርስና የአረባብ ልምዱን ለማሻሻልና ምርትና ምርታማነቱ እንዲያሳድግ የመፍትሔ አማራጮችን እያፈለቀ ለተግባራዊነቱም  የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አቶ ወርቁ ጠቁመዋል፡፡

ኘሮጀክቱ  የአየር ንብረት ለውጥን በማስተካከል ከካርቦን ሽያጭ በሚገኘው ገቢ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ  አላማ አድርጎ እየሰራ መሆኑን በማከል።

ከተጠቃሚ አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ተጠቃሚ ለመሆን  እንደሚተጉ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡- አሳምነው አትርሳው – ከቦንጋ ጣቢያችን