ኤሲ ሚላን የወለደው ኢንተርሚላን
በእግርኳሱ ዓለም የሁለቱ ቡድኖች የእርስ በእርስ ግንኙነት ትልቅ ትኩረት ከሚሰጣቸው የአንድ ከተማ (የደርቢ ) ግጥሚያዎች መካከል ከቁንጮዎች ተርታ ይመደባል ። ደርቢ ዴላማዶኒና ደግሞ የሁለቱ ቡድኖች የእግርኳሱ ፍልሚያ የእርስ በእርስ ግንኙነት መጠሪያው ነው ።
ከሁለቱ ክለቦች ኤሲ ሚላን በመመስረት ይቀድማል ። እንደ አዉሮፓዊያን አቆጣጠር በ1889 ነዉ የተመሰረተው ። ኤሲ ሚላን በተመሰረተ በ 10 ዓመታት ዉስጥ 3 የሴሪያ ዋንጫዎችን አነሳ ።
በ 1907 ግን ሚላን ከባድ ፈተና ገጠመዉ ። የሃገሪቱ እግርኳስ ማህበር የጣሊያን ተወላጆች ብቻ በኤሲ ሚላን ይጫወቱ የሚል ህግ አወጣ ።ይህን ህግ ያወጣዉ ክለቦች የዉጭ ሃገር ተወላጆችን እንዳያስፈርሙ ለማድረግ በማለም ነዉ።
ኤሲ ሚላን የወጣውን ህግ ተቃወመ ። በመቃወም ብቻ አላቆመም ፣ በሚቀጥለው የዉድድር ዓመት በሴሪአዉ ላለመጫወት ወሰነ ።
ከአርባ በላይ የሆኑ አመራሮች ክለቡን ለቀቁ ። እነዚህ አባላት የሌላ ሃገር ተወላጆች ከጣሊያን ተወላጆች ጋር በጋራ ሆነው መጫወት የሚችሉበትን ክለብ ማፈላለግ ጀመሩ ። የዚህ ስብብ መሪ ጂዮርጂዮ ሙጊያኒ ይባላል ። በእሱ መሪነት አዲስ የእግርኳስ ክለብ ተመሰረተ ። መጠሪያዉም ኢንተርናሲዮናል ተሰኘ ። እኛ ከዓለም የተዉጣጣን ወንድማማቾች ነን እንደማለት ነዉ ።
ጂዮርጂዮ ሙጊያኒ በጣሊያን በሰሜናዊቷ የሃገሪቷ ክፍል የኤሲ ሚላን ባላንጣ የሆነ ኢንተርሚላን የተሰኘ የእግርኳስ ክለብ መመስረቱን ለዓለም ህዝብ አወጁ ።
ሁለቱ የሚላን ከተማ ክለቦች አንድ እስታዲየም ይጠቀማሉ ። 80 ሺህ ተመልካች የመያዝ አቅም ያለዉን እና በጣሊያን ከሚገኙ ግዙፍ ስታዲየሞች መካከል አንዱ የሆነውን ሳንሴሮን። በዚህ የተነሳ በሴሪያዉ ሁለቱ ቡድኖች በተመሳሳይ ቀን በሜዳቸዉ እንዳይጫወቱ ይደረጋል ። በደርቢ ዴላማዶኒና ወቅት ባለሜዳ ሆኖ የሚጫወተዉ ቡድን ደጋፊ ከፍተኛ ወደ እስታዲየም የመግቢያ ትኬት ያገኛል ።
የመጫወቻ ሜዳዉ ሳንሴሮ አስቀድሞ የሚላን ሆኖ ነዉ የተገነባው ። 1925 የተገነባበት ዓመተ ምህረት ነዉ ። ኢንተርሚላን የዛኔ አሬና ሲቪካ የተሰኘ ትንሽዬ እስታዲየምን በሜዳዉ ሲጫወት ይጠቀም ነበር ። 10 ሺህ ተመልካች የመያዝ አቅም ነዉ ያለው ። እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ከ1947 ጀምሮ ግን ሁለቱ የሚላን ከተማ ክለቦች ሳንሴሮን በጋራ እንዲጠቀሙ ተደረገ ።
አንድን እስታዲየም በጋራ የሚጠቀሙ ብቸኛ ክለቦች ግን አይደሉም ።ልክ እንደ እንተርሚላን እና ኤሲ ሚላን አንድን እስታዲየም በጋራ የሚጠቀሙ ቡድኖች አሉ ።
ለአብነት ያህል በጣሊያን ሮማ እና ላዚዮ በተመሳሳይ ስታዲዮ ኦሎምፒኮን ከ 1953 አንስቶ በጋራ ይጠቀማሉ ። 72 ሺህ ስድስት መቶ ዘጠና ስምንት ተመልካች የመያዝ አቅም አለው ።
በዛዉ በጣሊያን ዉስጥ ጄኑዋ እና ሳምፕዶሪያም እስታዲዮ ሉይጂ ፌራሪን በጋራ ይጠቀማሉ ።
ከጣሊያን ዉጪ አንድን እስታዲየም በጋራ የሚጠቀም ክለብ እና ብሔራዊ ቡድን አለ ። በሆላንድ አያክስ በሜዳዉ ሲጫወት ዩሃይን ክራይፍ አሬናን ይጠቀማል ። የኔዘርላንድ ብሄራዊ ቡድንም ባለሜዳ ሲሆን ይህንን ሜዳ ነዉ የሚጠቀመው ።
በሲዉዲን አይኬ ፉትቦል እና ብሄራዊ ቡድኑ በእስቶኮልም የሚገኘውን ፍሬንድስ አሬናን በጋራ ይጠቀማሉ ።
አዘጋጅ ፡ ሙሉቀን ባሳ
More Stories
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የጅቡቲ አቻውን 6ለ1 አሸነፈ
ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ የምስክር ወረቀት ተሰጠው
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ከአፍሪካ 1ኛ ከዓለም 3ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች