የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው
ሀዋሳ፡ ግንቦት 30/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 2ኛ ዙር 10ኛ አመት 37ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው፡፡
የወልቂጤ ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ አቶ ሸምሱ በሽር በዚህ ወቅት እንዳሉት የልማት፣ የሰላም፣ የዲሞክራሲ ሥርዓት እና የመልካም አስተዳደር ግንባታ እውን እንዲሆን ምክር ቤቱ የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል።
በጉባኤው ላይ የ2015 ዓ.ም የ9 ወራት አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው በበኩላቸው ስራ አጥ ዜጎችን በመለየት በተለያዩ ዘርፎች 4ሺ 903 የህብረተሰብ ክፍሎችን የስራ ባለቤት ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በከተማው በሚገኙ 32 ትምህርት ቤቶች ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እየተሰራ ነው ሲሉም ተናግረዋል ።
የብድር አመላለስ፣ ገቢ አሰባሰብ፣ የሼድ ግንባታና አጠቃቀም ጉድለቶች በስፋት በምክር ቤቱ በስፋት ተነስቷል።
የከተማ ግብርና በተለይም የወተት አቅርቦት፣ የሴፍቲኔት ድጋፍ፣ የቆሻሻ አወጋገድ፣ ሰላም የሚያውኩ አካላት ተጠያቁነት ዙርያ እንዲሁም የመንግስት ንብረት አስተዳደር ችግሮች ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውን አባላቱ ተናግረዋል።
በወልቂጤ ከተማ የተጀመረው ሳምንታዊ የገበያ ማእከል ግንባታ መጓተት፣ የከተማው እግር ኳስ ክለብ ቀጣይነት ባለው መልኩ አለመደገፍ ፣ በትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ደላሎች መብዛትን የተመለከቱ ጥያቄዎችን አባላቱ አንስተዋል።
በከተማው በየደረጃው የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በአገልጋይነት ስሜት የሚንቀሳቅስ ታማኝና በእውቀት ላይ ተመስርቶ የሚሰራ አመራር መገንባት እንደሚገባ ነው የገለጹት።
ለተነሱት አስተያየትና ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት አቶ እንዳለ ስጦታ በቅድሚያ በከተማው የሚነሱ የውሀ እንዲሁም የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ተጀምረውና ተቆፋፍረው የሚገኙ መንገዶችን ለማስጨረስ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ከጌጠኛ ድንጋይና ከዲች ግንባታ የጥራት ክፍተቶች ለማሻሻል እና ጥፋተኞችን ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚሰራም አመላክተዋል።
የህዝቡን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶች ማገዝ ይገባልም ብለዋል፡፡ በተለያየ አጀንዳ ተጠምደው ልማትን የሚያደናቅፉ አካላትን ለህግ አሳልፎ መስጠት እንደሚገባም ነው ከንቲባው ያሳሰቡት።
ዘጋቢ፡ እንዳልካቸው ደሳለኝ- ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የግብርናን ምርትና ምርታማነት ማዘመንና ማሳደግ ዘላቂ ልማትን እና የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባሻገር የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑ ተጠቆመ
ባለፉት አራት አመታት በክልሉ 270 የውሃ ኘሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ከ450 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተገለጸ
ግሎባል ፋይናንስ ባካሄደው የ2025 ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ የባንኮች ውድድር አዋሽ ባንክ ከ36 የአፍሪካ ምርጥ ባንኮች አንዱ በመሆን እውቅና ማገኘቱ ተገለፀ