“የዩንቨርሲቲውን ደረጃ የማሻሻል ስራ ሰርተናል” – ዶ/ር ሀብታሙ አበበ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት

“የዩንቨርሲቲውን ደረጃ የማሻሻል ስራ ሰርተናል” – ዶ/ር ሀብታሙ አበበ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት

የዛሬ የንጋት እንግዳችን ዶክተር ሀብታሙ አበበ ይባላሉ፡፡ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ናቸው፡፡ በዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡን እንግዳ አድርገናቸዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

በመለሰች ዘለቀ

ንጋት፡- ለቃለ መጠይቃችን ፈቃደኛ ስለሆኑ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ።

ዶክተር ሀብታሙ፡- እኔም ስለሰጣችሁኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡

ንጋት፡- ዶክተር ሀብታሙ ማን ናቸው?

ዶክተር ሀብታሙ፡- ተወልጄ ያደኩት በሀዲያ ዞን ምሻ ወረዳ ሰሜን ዋስገበታ ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ አስተዳደጌ እንደማንኛውም የገጠር ልጅ በጨዋታና በስራ ቤተሰቤን በማገዝ ነው፡፡ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ትምህርቴን በዋስገበታ አንደኛና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተከታተልኩት። ከዘጠነኛ እስከ አስረኛ ክፍል ሞርሲጦ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትያለሁ፡፡ አስረኛና አስራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርቴን ደግሞ በዋቸሞ ሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤት ነበር የተማርኩት። በትምህርትም ጎበዝ ከሚባሉ ተማሪዎች አንዱ ነበርኩ፡፡

የመጀመሪያ ድግሪዬን በዲላ ዩኒቨርሲቲ በኬሚስትሪ ትምህርት ክፍል ተከታትያለሁ። በመቀጠልም ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ በምስራቅ ባደዋቾ/ሾኔ/ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በመምህርነት አገልግያለሁ፡፡

ሁለተኛ ድግሪዬን በኦርጋኒክ ኬሚስትሪ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተቀብያለሁ፡፡ ከዚያም በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ስሰራ ቆይቻለሁ፡፡ በመቀጠልም በዝውውር ወደ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አቀናሁ። በ2004 ዓ.ም ደግሞ ወደ ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ተዛወርኩ፡፡ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው የትምህርት መርሃ ግብሮችና ጥራት ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር ሆኜ ለሁለት አመታት አገልግያለሁ፡፡ ከዚያም የሶስተኛ ድግሪዬን በህንድ ሀገር በተመሳሳይ ሙያ ተከታትያለሁ፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በዛው ህንድ ሀገር ባገኘሁት የትምህርት እድል የተለያዩ የአመራር ስልጠና ወስጃለሁ፡፡ ወደ ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ተመልሼ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ሆኜ እያገለገልኩ ሳለ የፕሬዝዳንትነት ውድድር ሲወጣ ተወዳድሬ አሸነፍኩ፡፡ ከ2011 ዓ.ም ሚያዚያ ወር ጀምሮ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሆኜ እያገለገልኩ እገኛሉ። ከዚህም ጎን ለጎንም የምርምር ስራዎችን እየሰራሁ እንዲሁም ከህንድ ሀገር “Phd” ወይም ሶስተኛ ድግሪዬን በማናጅመንት ትምህርት መስክ “በኦንላይን” እየተከታተልኩ ነው፡፡

ንጋት፡- ስለ ዩኒቨርሲቲው አመሰራረትና አጠቃላይ ገጽታ ቢገልጹልን?

ዶክተር ሀብታሙ፡- ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የተመሰረተው በ2004 ዓ.ም ነው። ዩኒቨርሲቲው የሶስተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ ነው የሚባለው፡፡ የሶስተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ ይባል እንጂ ስፋቱ፣ የተማሪዎችና የትምህርት ክፍሎች ብዛትና ግዝፈቱ ከሌሎች የሶስተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች ለየት ያደርገዋል፡፡ ከ32 ሺህ በላይ ተማሪዎችና ከ6 ሺህ 700 በላይ ሰራተኞች በሶስቱም ኮሌጆች ይገኛሉ፡፡ ከሶስቱም ኮሌጆች ውጪ ስምንት የሚሆኑ የምርምር ማዕከላት ይገኛሉ። ስምንት የማስተማሪያ ማዕከላት አሉ። እነዚህም ከሶስተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ አንደኛ ትውልድ እንዲቀርብ የሚያስችሉ ተግባራት ናቸው፡፡

ንጋት፡- በዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማሩን ስራ ውጤታማ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ምን ይመስላሉ?

ዶክተር ሀብታሙ፡- የመማር ማስተማሩን ስራ ውጤታማ ለማድረግ ትኩረት አድርገን የምንሰራቸው ስራዎች አሉ፡፡ ይህንንም ለማሳካት የምንመራበት የአመራር ስልት ቀይሰን ነው የጀመርነው። የአመራር ስልታችን የተቀናጀ የአመራር ስርዓት ነው የምንከተለው፡፡ ሁሉም ተቋማት በሁሉም ዘርፎች እራሳቸውን  ችለው እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ተቋማት በጠንካራ የአሰራር ስርዓት እንዲመሩ የማድረግ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ጠንካራ ተቋማት በሚኖሩበት ጊዜ ጠንካራ ሀገር ስለሚኖር እኛም በተቋማት ግንባታ ላይ ትኩረት አድርገን ነው እየሰራን ያለነው፡፡

የተቋም ግንባታ ተግባር አራት ጉዳዮችን ያካትታል፡፡ አንደኛው ቁሳቁስ ማሟላት፣ የማስተማሪያ የቤተሙከራ፣ የህክምና ቁሳቁሶች የማሟላት ስራ ሰርተናል፡፡ ሁለተኛ እነዚህን ቁሳቁሶች መሸከም የሚችል የመሰረተ ልማት ዝርጋታን ማሟላት። በመቀጠል የሰው ሀብት ማልማት ላይ ጠንካራ ስራ ሰርተናል፡፡ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ 2011 ዓ.ም ላይ ከስምንት ያልበለጡ የፒኤችዲ(phd) ዶክተሮች የነበሩት ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ትምህርት ላይ ያሉትንም ጨምሮ ከ178 በላይ ፕሮፌሰሮችና ረዳት ፕሮፌሰሮች ይገኛሉ፡፡

እንደ ሀገር የተያዘውን የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ በ2022 ዓ.ም 75 ከመቶ ሁለተኛ ድግሪ ያላቸው፣ 25 ከመቶ ፒኤችዲ(phd) ዶክተሮችን ለማድረስ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ጊዜ 85 ከመቶ ሁለተኛ ድግሪና 15 ከመቶ ፒኤችዲ(phd) ዶክተሮች ማድረስ ተችሏል፡፡ ይህንን ለማሳካት በሁለት አመት ብቻ 40 የሚሆኑ መምህራንን ለሶስተኛ ድግሪ ወደ ህንድ ሀገር ልከናል፡፡

ይህም ብቻ ሳይሆን የአስተዳደር ሰራተኞችም በትምህርት ራሳቸውን እንዲያበቁ ለማድረግ በግቢ ውስጥ ባሉ ፕሮግራሞች ላይ በሳምንት መጨረሻና በማታ መርሃ ግብር ትምህርታቸውን እንዲማሩ እየተደረገ ነው፡፡ ስለሆነም የሰው ሀብት ልማት ላይ ውጤታማ ስራ ሰርተናል ማለት ይቻላል፡፡

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ላይ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል። የመማሪያ ክፍሎችን በጣም ዘመናዊ የማድረግ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ለእያንዳንዱ ተማሪ የራሱ ዴስክ ቶፕ ኮምፒዩተር እንዲዳረስ የማድረግ ስራ ተሰርቷል፡፡ ምርምሮቻችን ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ፣ መማር ማስተማሩ የትምህርት ጥራቱን በጠበቀ መልኩ የሚሄድበትን ስርዓት ለመዘርጋት በዚህ አመት ጠንካራ ስራ ሰርተናል፡፡

በአጠቃላይ የመማር ማስተማሩ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎቻችን አራቱን የተቋም ግንባታን መሰረት ያደረጉ እንዲሆኑ አድርገን ስራዎችን እየሰራን እንገኛለን፡፡ 460 ኮምፒዩተሮች በዘመናዊ ሁኔታ በአራት ቤተሙከራዎች ላይ ተደራጅተዋል። በዚህም አንድ መምህር በአንድ ክፍል ውስጥ ሲያስተምር ለአስራ አምስት ክፍሎች ማስተማር የሚችል አስራ አምስት “ስማርት ክፍል” የሚባሉ አሉ፡፡

ንጋት፡- በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ከባቢን ለመፍጠር ምን ምን ተግባራት ተከናውነዋል?

ዶክተር ሀብታሙ፡- ሰላማዊ የመማር ማስተማር ከባቢን ከመፍጠር አንጻር በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የጎላ የጸጥታ ችግሮች ተስተውሎ አያውቅም፡፡ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የጸጥታ ችግሮች በነበሩባቸው ወቅቶችም ቢሆን በዩኒቨርሲቲው የጸጥታ ችግሮች አልተከሰተም፡፡ ይህም የአካባቢው ማህበረሰብ ሰላም ፈላጊ በመሆኑና ለተቋሙ ካለው መልካም እይታ የተነሳ ነው፡፡

የአካባቢው ወጣቶች፣ የግቢው ማህበረሰብና ተማሪዎች ሰላም ለማስጠበቅ በቅንጅት ይሰራሉ፡፡ ሰላም የዩኒቨርሲቲያችን አርማ በመሆኑ ሁሉም ሰው ለሰላም ትኩረት እንዲሰጥ በግቢው መግቢያ ላይ “የሰላም ማዕከል” የሚል አርማ ተቀምጧል፡፡ ችግሮች ሲኖሩ በውይይት ወደ ሚመለከተው አካል በመቅረብ ይፈታል እንጂ ለሰላም መደፍረስ ምክንያት ሊሆን አይችልም የሚል መርህ ይዘን ነው እየሰራን የምንገኘው፡፡ የዞን አስተዳደር፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ ተማሪዎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ በትኩረት ይሰራሉ፡፡ ከዚህም የተነሳ በዩኒቨርሲቲው ጠንካራ የሰላም እሴት ገንብተናል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ንጋት፡- በዩኒቨርሲቲው ብዝሃነትን ከማስተናገድ አንጻር ምን እየተሰራ ነው?

ዶክተር ሀብታሙ፡- በዩኒቨርሲቲዎች ብዝሃነትን ማስተናገድ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን ለማሳካት በተግባር በርካታ ስራዎችን እንሰራለን፡፡ የሀይማኖት ብዝሃነትን ከማስተናገድ አንጻር ተማሪዎች የየራሳቸውን ሀይማኖት እንዲከተሉና እንዲያመልኩ ይፈቀዳል። አንድ ሰው በመንፈሳዊ፣ በአካላዊ እንዲሁም በእውቀትም እንዲያድግ ይፈለጋል። በመሆኑም ሀይማኖተኛ ሳይሆን ፈጣሪውን የሚፈራ ማህበረሰብ እንዲገነባ እንፈልጋለን።

በግቢው ውስጥ ከአለባበስ ጀምሮ ሀይማኖታዊነትን ማንጸባረቅም ይሁን መስበክ አይፈቀድም፡፡ የብሄር ብዘሃነትን ከማስተናገድ አንጻር ከተማሪዎች ማደሪያ ድልደላ ጀምሮ የተሰባጠረ እንዲሆን ይሰራል። ከሰራተኞች ጋር ተያይዘው ብዙም ችግር የሚታይበት አይደለም። መምህራኖቻችን ከሁሉም የሀገራችን ክፍሎች የተሰባጠሩ ናቸው፡፡ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅምና የትምህርት እድገት በሚኖርበት ጊዜ በተቻለን መጠን ፍትሃዊ እንዲሆን እንሰራለን፡፡ ዩኒቨርሲቲ ሀገር ማለት ስለሆነ ብዘሃነትን ማስተናገድ ላይ በትኩረት እየሰራን እንገኛለን፡፡

ንጋት፡- የሴቶችን ተሳትፎ ከማሳደግ ረገድስ ምን ምን ስራዎች ተሰርተዋል?

ዶክተር ሀብታሙ፡- የሴቶችን ተሳትፎ ከማሳደግ አንጻር በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ያሉ ሴቶች በብዛት የበቁ ናቸው፡፡ በዩኒቨርሲቲው የኃላፊነት ቦታዎች ላይም ፍላጎት ያላቸው ሴቶች ተወዳድረው እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥሯል፡፡ በቅጥር ጊዜም የሲቪል ሰርቪስ ህግን ተከትለን እንሰራለን፡፡

ከሌሎች ተመራማሪዎች ጋር ተወዳድረው ከሚያገኙት በተጨማሪ ለሴት ተመራማሪዎች በተለየ ሁኔታ በጀት ይበጀታል፡፡ በኃላፊነት ቦታዎችም በመመሪያው መሰረት ማበረታቻ ይደረጋል። በአስተዳደር ዘርፍም ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ ድጋፍ ይደረጋል፡፡ ለሴት ተማሪዎችም በተለየ ሁኔታ ድጋፎች ይደረጋሉ፡፡

ንጋት፡- ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ መስኮች ላደረገው አስተዋጽኦ የተገኙ ማበረታቻዎች ካሉ ቢገልጹልን?

ዶክተር ሀብታሙ፡- ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በ2004 ዓ.ም በጥቂት ሰራተኞች፣ ተማሪዎችና መምህራን ስራ የጀመረ ተቋም ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ብዙ ርቀት ተጉዟል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የሶስተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ ይባል እንጂ የአንደኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ ስራ ነው እየሰራ ያለው፡፡ ለዚህም ትልቁ ምክንያት የሆነው ዩኒቨርሲቲው ያለበት አካባቢ ለብዙ ዞኖችና ልዩ ወረዳ አጎራባች በመሆኑ እንደ ማእከል ያገለግላል፡፡

የትምህርት ፈላጊዎች ቁጥር በጣም ብዙ ነው፡፡ ለዚህም ነው በአስር አመት እድሜ ውስጥ ከ32 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ማፍራት የተቻለው፡፡ ከዚህም ባሻገር በመደበኛና በተከታታይ የምናስተምራቸው ተማሪዎች ቁጥር እኩል ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የለውጡን መርህ ተከትሎ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል።

በዚህም በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ማበረታቻ ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡ ከዚህም ውስጥ በ2013 ዓ.ም በተለያዩ መስፈርት በሀገር ደረጃ ካሉ 25 ዩኒቨርሲቲዎች ግንባር ቀደም በመሆን ተሸልሟል፡፡ በዚም ፕሬዝዳንቱም ከ25 ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች ጋር ተወዳድሮ ተሸልሟል፡፡ በዛው አመት የንግስት እሌኒ ኮምፕሬንሲቭ ሆስፒታል በሀገሪቱ ካሉ ሆስፒታሎች ጋር ተወዳድሮ 10 ከተመረጡት ውስጥ አንዱ ስለነበር የዋንጫ፣ የሰርተፊኬትና የ3 ሚሊዮን ብር ተሸላሚ ሆኗል፡፡

በዛው አመት በኮቪድ መከላከያ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ግንባር ቀደም በመሆን ሁለት ጊዜ ከደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደርና ጤና ቢሮ ሽልማት ተቀብሏል። በዛው አመትም ለአካባቢ ማህበረሰብ ባበረከተው አስተዋጽኦ ከዞኑ አስተዳደርና ከዞኑ ልማት ማኅበር ሽልማት ተቀብሏል። ይህም ብቻ ሳሆን በተለያዩ ጊዜያት ዩኒቨርሲቲው በሚሳተፊባቸው ጉዳይ ላይ ከተለያዩ መንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የማበረታቻ ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡

ንጋት፡- ጊዜዎትን ሰጥተው ስለሰጡን ማብራሪያ በድጋሚ አመሰግናለሁ።

ዶክተር ሀብታሙ፡- እኔም ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡