የጎፋ ዞን ፕላንና ልማት መምሪያ ለዞኑ ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግና ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው አራት መጽሐፍትን አሳትሞ አስመረቀ

መምሪያው የሰባት ዓመት ፍኖተ-ብልጽግና መሪ የልማት ዕቅድ፣ የ2016 ዓም አብስትራክት መጽሐፍ፣ የተቋሙ የሰባት ዓመት ዕቅድ እና የስነ ህዝብ ጉዳዮች የሰባት ዓመት የልማት ዕቅድ መጽሐፍ አሳትሞ አስመርቋል።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ መምሪያው ያሳተመው መጽሐፍ ቀደም ሲል በዞኑ የሚታየውን የተደራጀ መረጃ ዕጥረት በመቅረፍ ዞኑ ከየት ተነስቶ ወደየት መድረስ እንዳለበት የሚመራ ዕቅድ መሆኑን ገልጸዋል።

የጎፋ ዞን ፕላንና ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሉቀን ጉጃ እንደገለጹት፤ መረጃ በአግባቡ በመሰብሰብና በጥራት ተንትኖ ህጋዊ በሆነ መንገድ ለሚመለከተው አካል ለማቅረብ መምሪያው በትኩረት መሰራቱን ተናግረው ባለድርሻ አካላት ከአንድ ማዕከል በሚያገኙት መረጃ ሥራዎችን በጥራት ለመሥራት ዝግጁ መሆን እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ኃላፊው አክለውም መሰረተ ልማት ተደራሽነትና ፍትሐዊነት ልዩ ድጋፍ በሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ መሆኑንም አንስተዋል።

ለመጽሐፍቱ ህትመት ከ420ሺህ ብር በላይ ወጭ መደረጉንም ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ የተሳተፉ አካላት በበኩላቸው፤ መምሪያው የተደራጀ መረጃ በማዘጋጀት መጽሐፍ በማሳተም ለሚመለከተው አካል ተደራሽ ለማድረግ ያከናወነው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።

በመድረኩ ለስራው መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ዕውቅና ተሰጥቷል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን