የ2017 ዓ.ም የ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ መሰጠት መጀመሩን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምርት ቢሮ ገለጸ
በክልሉ ከ120 ሺህ በላይ የ6ኛ ክፍል ተማሪዎች እንደሚፈተኑም ተገልጿል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምርት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ፀሃይ ወራሳ በጋሞ ዞን አርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ቆላ ሼሌ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተው ፈተናውን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት፤ የትምህርት ውጤታማነትን ለማሳደግ ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ስራ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው እንደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 120 ሺህ 800 የ6ኛ ክፍል ተማሪዎች ክልል አቀፍ ፈተና በመፈተን ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
የፈተናው ደህንነት እንዲጠበቅ ቅንጅታዊ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ያነሱት ኃላፊዋ፤ ተማሪዎች ተረጋግተው ፈተናቸውን እንዲፈተኑና የሚመለከታቸው አካላትም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ(ዶር) እንደገለጹት፤ ዞኑ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን ተጨባጭ የድጋፍና ክትትል ስራዎች ሲያከናወኑ መቆየታቸውን በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ የቆላ ሼሌ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተው ፈተናውን ባስጀመሩበት ወቅት ገልጸዋል::
የጋሞ ዞን ትምርት መምሪያ ኃላፊ አዲሱ አዳሙ (ዶር) በበኩላቸው፤ በ2017 ዓ.ም የትምርት ውጤታማነትን ለማሻሻል በመምህራን ልማት ዘርፍ ብሎም ተማሪን ለማብቃት ሰፋፊ ተግባራት መከናወናቸውን ገለፀዋል።
ለ6ኛ ክፍል ክልላዊ የፈተና ተፈታኞች፣ አስፈታኞች እና ሱፕርቫይዘሮች አስፈላጊው ኦሬንቴሽን መሰጠቱን አስታውሰዋል።
የፈተና አስተዳደር ሥርዓትን የጠበቀና ከኩረጃ የጸዳ ፈተና ለመስጠት በትኩረት ሲሰራ መቆየቱንም ሃላፊው አክለዋል።
በዞኑ ትምህርት ቤቶች 29 ሺህ 575 ተማሪዎች በ199 መፈተኛ ጣቢያዎች ሰላማዊ በሆነ መንገድ በመፈተን ላይ እንደሚገኙም ዶክተሩ አክለው ገልጸዋል።
ዘጋቢ: አሰግድ ተረፈ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን

More Stories
የቡርጂ ዞን ምክር ቤት አቶ ትንሳኤ ዮሐንስ ወጌ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አድርጎ ሾመ
የወባ በሽታ ስርጭትን የመከላከልና የመቆጣጠርን ጉዳይ ቀዳሚ ተግባር አድርጎ እየሰራ መሆኑን የስልጤ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ
አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን ተገልጋዩን ለማርካት እየሰራ መሆኑን የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል አስታወቀ