የማንጎን ምርትና ምርታማነት በማሳደገ የአምራች አርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለፀ

‎ስነ ምህዳርን ያገናዘበ የተቀናጀ የማንጎ ምርትና ምርታማነት ማሻሻያ ፕሮግራም ዙሪያ በአርባምንጭ እና አካባቢው ለተደራጁ ኢንተርፕራይዞች የክህሎት ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።

‎በስልጠናው መክፈቻ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊና የግብርና ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሻምበል ቦኩ፤ በዞኑ ወጤታማ በሆኑ የግብርና ዘርፎች ወጣቶችን በማደራጀት ተጠቃሚ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል።

‎በተለይ ዋነኛ ሀብት የሆነውን መሬት በአግባቡ ለመጠቀም መንግስት ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ባሻገር ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አይነተኛ ሚና ይጫወታሉ።

ኤስፒኤ የተሰኘው ድርጅት ጨዋማ፣ ተዳፋት እና ድንጋያማ መሬቶችን ወደ ጥቅም በተጨባጭ በመቀየር በምዕራብ አባያ ወረዳ በወጣቶች ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበ ይገኛል ሲሉም አብራርተዋል።

‎የጋሞ ዞን ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ታፌ ታደሰ መድረኩን በንግግር ሲከፍቱ እንዳሉት፤ በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገራት ለወጣቱ የስራ ዕድል ለመፍጠር የብድር አገልግሎት ከማመቻቸት ባለፈ ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ጋር በመቀናጀት የክህሎት መር ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

‎በዞኑ የማንጎ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር የስራ ፈጠራና ፈጣሪነትን ክህሎት ለማጎልበት እየተሰራ እንደሚገኝ ኃላፊው ጠቁመው በዚህም ለውጥ መገኘቱን አውስተዋል።

‎ስልጠናው የማንጎ እሴት ሰንሰለትን በመጠቀም የማንጎ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የማንጎ አምራች ስነ ምህዳርን ያገናዘበ የተቀናጀ የማንጎ ምርትና ምርታማነት ማሻሻያ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ባዩ እንቻለው ናቸው።

‎ስልጠናውን ዓለም አቀፍ የስነ ነፍሳት እና ስነ ምህዳር ምርምር ማዕከል (icipe) የተሰኘ የምርምር ተቋም ስር የሚገኝ (An Integrated Agro Ecological Approach to Mango production) በአርባ ምንጭና አካባቢው በማንጎ ልማትና እሴት ሰንሰለት የስራ ፈጠራና ስራ ፈጣሪነት ዙሪያ እየሰጠ ይገኛል።

‎ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን