ውጤታማ የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓትን ተግባራዊ በማድረግ የልማት ስራዎችን ለማፋጠን ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ገለጸ

ቢሮው ለአየር ንብረት ለውጥና መሬት አስተዳደር ፕሮግራም አስተባባሪዎች፣ ለወረዳ ፋይናንስ ፎካሎች፣ ለግዢ ባለሙያዎች እና ለህብረት ስራ ኦዲተሮች ሁለተኛ ዙር ሥልጠና በወልቂጤ ከተማ ሰጥቷል።

የመሬት አቀማመጥን መሰረት ያደረገ የአየር ንብረት ለውጥ ትግበራ ፕሮግራም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ መቀነስ፣ የግብርና ምርታማነትን መጨመር፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እና ድርቅን መቋቋም የሚሉት ተልዕኮዎች አሉት።

በአለም ባንክና በፌደራል መንግስት የበጀት ድጋፍ የሚተገበረው ይህ ፕሮግራም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም 66 ወረዳዎችን ተደራሽ ያደርጋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ በመንግስት ፋይናንስ ዘርፍ የቻናል አንድ ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታረቀኝ ኑራሙ እንዳሉት፤ ፕሮግራሙ የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠራል።

ውጤታማ የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓትን ተግባራዊ በማድረግ የልማት ስራዎችን ለማፋጠን ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት አቶ ታረቀኝ፤ የፕሮግራሙ የፋይናንስ አጠቃቀምና አስተዳደር ሥርዓትም የመንግስትን የሒሳብና የበጀት አስተዳደር ሥርዓትን በተከተለ መልኩ መፈጸም እንዳለበት ጠቁመዋል።

የተዘጋጀው ሥልጠናም የሒሳብ፣ የግዢና የኦዲተር ባለሙያዎች የክልሉ መንግስት ያወጣቸው የፋይናንስ አስተዳደር አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎችን ተፈጻሚ በማድረግ በኩል ያለባቸውን ክፍተቶች በመሙላት የክልሉን አፈጻጸም ከፍ ለማድረግ እንደሚረዳም ገልጸዋል።

አቶ ጥበቡ ፍሬው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ የአየር ንብረት ለውጥና መሬት አስተዳደር ፕሮግራም ከፍተኛ የሒሳብ ባለሙያ ናቸው።

ፕሮግራሙ በአየር ንብረት ለውጥ ያልተበገረ ኢኮኖሚ በመገንባት የአርሶ አደሩን ምርታማነት ማሳደግ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ጠቁመው፤ የሥልጠናው አላማም የፕሮግራሙን ሒሳብ ማዘመን እንዲሁም ከዚህ በፊት ይስተዋሉ የነበሩ ክፍተቶችን ለማረም ስለመሆኑም ተናግረዋል።

ወ/ሮ እፀገነት ጀማል በስልጤ ዞን የዳሎቻ ወረዳ ግዢና ክፍያ የሥራ ሂደት አስተባባሪ ሲሆኑ አቶ ዘመነ አዲሴ ደግሞ በሀዲያ ዞን ዱና ወረዳ የአየር ንብረት ለውጥና መሬት አስተዳደር ፕሮግራም የሒሳብ ባለሙያ ናቸው። በሰጡት አስተያየትም ፕሮግራሙ በመሬት አያያዝና በአየር ንብረት ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ የሚገኝ ፕሮግራም ነው ብለዋል። በሥልጠናውም ከሒሳብና ግዢ ሥርዓት ጋር በተያያዘ የነበራቸውን እውቀት የሚጨምር ግንዛቤ እንዳገኙም ተናግረዋል።

ለሁለት ቀናት በቆየው በሁለተኛው ዙር ሥልጠና ከስልጤ፣ ከሀዲያና ከከምባታ ዞኖች የተውጣጡ የፕሮግራሙ አስተባባሪዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፡ ተረፈ ሀብቴ – ከወልቂጤ ጣቢያችን