ግብርን በታማኝነት በመክፈል ግዴታቸውን ለተወጡ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
“ታማኝ ግብር ከፋይ የልማት አርበኛ ነው” በሚል መሪ ቃል በ2016 በጀት ዓመት ግብርን በታማኝነት ለከፈሉ ግብር ከፋዮች የዕውቅና እና የሽልማት መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ፤ ባለፉት አመታት በክልሉ ለተገኘው ሰላምና ልማት የግብር ከፋዩ ሚና የጎላ መሆኑንና በቀጣይም ይበልጥ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በሂደቱ ግብር ከፋዮች ችግሮች ቢገጥሟቸው እንኳ የክልሉ መንግስት ከጎናቸው ሆኖ ችግራቸውን ለመቅረፍ እደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የክልሉ መንግስት የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና ቀልጣፋ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራትንና ንቅናቄዎችን እያካሄደ መሆኑንም አመላክተዋል።
መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና የተገልጋዮችን እርካታ ለማሳደግ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ ነውም ብለዋል።
ግብርን በታማኝነት በመክፈል ሌብነትን መፀየፍ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የንግዱ ማህበረሰብ ህግን ተከትሎ መስራትና ግዴታቸውን መወጣት እንደሚኖርባቸውና የመንግስት አገልግሎት ሰጪ አካላትም ሌብነትን ተፀይፈው መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
ለዚህም መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልፀው በታማኝነት ግብርን ለከፈሉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
ግብርን በፍቃደኝነት መክፈል የዜግነት ግዴታን መወጣት ብቻ ሳይሆን የስልጣኔና አገር የመውደድ ምልክት መሆኑን የገለፁት ደግሞ የሲዳማ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን ኃላፊ አቶ ደምሴ እሳቱ ናቸው።
በ2016 በጀት አመት ግብርን በታማኝነት የከፈሉ 53 ታማኝ ግብር ከፋዮች መኖራቸውን አንስተው ሁለት የመንግስት የልማት ተቋማት መኖራቸውን አስገንዝበዋል።
በመገባደድ ላይ በሚገኘው 2017 በጀት ዓመት 11 ወራት 12.4 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻላቸውንም ገልፀዋል።
በመድረኩ 2 ሚሊዮን ብር እና ከዚያ በላይ ግብር የከፈሉ ግብር ከፋዮች የዋንጫ፣ የሜዳልያና የሰርተፊኬት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ዘጋቢ፡ ቤተልሄም ለገሰ
More Stories
ውጤታማ የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓትን ተግባራዊ በማድረግ የልማት ስራዎችን ለማፋጠን ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ገለጸ
የማንጎን ምርትና ምርታማነት በማሳደገ የአምራች አርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለፀ
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የሱፐርቪዥን ልዑካን ቡድን በሀላባ ቁሊቶ የከተማ ልማት ስራዎችን ጎብኝቷል