በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳሰበ

በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳሰበ

ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃትን፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን እና የህጻናት ጉልበት ብዝበዛን ለመከላከልና ለማስቆም የተዘጋጀ የንቅናቄ መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢፌዴሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሒክማ ከይረዲን፤ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ቀበሌ በተከናወኑ ስራዎች የተሻለ ለውጥ ቢመዘገብም አሁንም በርካታ ተግባራት እንደሚጠበቁ ጠቁመዋል።

በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል በርካታ የፖሊሲ፣ የህግ ማዕቀፎችና የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ አብራርተዋል።

እንደሀገር በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስቆምና ለማስወገድ የተያዙ እቅዶችን በጋራ ለማሳካት የሁሉንም ትብብር እንደሚጠይቅ አሳስበዋል።

ሴቶች በማህበረሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ማህበራዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው የገለጹት ደግሞ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ገነት መኩሪያ ናቸው።

ሠላምን ለማረጋገጥና ለልማት የሚያደርጉት አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን በመጠቆም፤ የሚደርሱባቸውን ጫናዎች ለመቀነስ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በመድረኩ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና በሀይል ጥቃት ሁኔታ ላይ የተዘጋጀ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ1 መቶ 40 በላይ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዳሉ በሰነዱ ተመላክቷል።

በኢትዮጵያም እየተፈጸሙ ያሉትን ድርጊቶች ለመከላከል ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ተቀብላ ተግባራዊ እያደረገች ነው ተብሏል።

በመድረኩ ከፌዴራል እስከ ዞን ድረስ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፡ አካሉ ወልደኢየሱስ – ከቦንጋ ጣቢያችን