የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ከ”ኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደር” ሀዋሳ ቅርንጫፍ ጋር በመተባበር በሀዲያ ለአምብቾ ጎዴ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ከ”ኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደር” ሀዋሳ ቅርንጫፍ ጋር በመተባበር በሀዲያ ለአምብቾ ጎዴ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 05/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ከ”ኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደር” ሀዋሳ ቅርንጫፍ ጋር በመተባበር በሀዲያ ዞን ሌሞ ወረዳ ለአምብቾ ጎዴ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚሆን ከ2 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ።

የተደረገው ድጋፍ የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅ አንፃር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑም ተጠቁሟል።

በድጋፍ አሰጣጥ መርኃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳዊት ሃየሶ፤ ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ማህበረሰብ ለመደገፍ “ኤስ ኦ ኤስ” ከሚባል ድርጅት ጋር በመተባበር ለሶስት አመታት የሚቆይ ፕሮጀክት ቀርፆ ወደ ተግባር ገብቷል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በትምህርት ቤቶች ብቻ ሳይሆን በማህበረሰብ ሁለንተናዊ ድጋፍ ይልቁንም በህፃናትና እናቶች ላይ ትኩረት ያደርጋል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ በዕለቱ ለአምብቾ ጎዴ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተደረገው ድጋፍ አንዱ አካል ነው ብለዋል።

ለትምህርት ቤቱ የተደረገው ድጋፍ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የገለፁት ዶ/ር ዳዊት፤ መምህራንን አጋዥ የሆኑ የትምህርት ቁሳቁሶችን ያካተተ መሆኑን ጠቁመዋል።

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር አበበ ሎላሞ፤ ዩኒቨርሲቲው የአምብቾ ጎዴና አካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮግራም ከኤስ ኦ ኤስ ሀዋሳ መንደር ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ፕሮጀክት ቀርፆ ወደ ተግባር መግባቱን ገልፀዋል።

በዕለቱም ለአምብቾ ጎዴ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 2 ሚሊየን 4 መቶ 82 ሺህ 2 መቶ ብር ወጪ በማድረግ የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጓል ነው ያሉት።

ፕሮጀክቱ በሶስት አመት ቆይታው በህፃናትና እናቶች ላይ ከሚሰራው ስራ በተጨማሪ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል፣ የመምህራን አቅም ማጎልበትና መሰል ስራዎችን እንደሚሰራም ዶ/ር አበበ ገልጸዋል።

የ”ኤስ ኦ ኤስ ህፃናት መንደር” አራዳ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ በላይ ይልማ፤ ድርጅቱ በተለየዩ ሀገራት በህፃናትና ሴቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ስራ እንደሚሰራ ገልፀው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን የተለያዩ ማህበረሰብ ተኮር ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በድጋፍ ስነ-ስርዓቱ የተገኙት የሌሞ ወረዳ ትምህርት ቤቶች ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አበበ፤ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የትምህርት ግብአቶች መሟላት አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ከ”ኤስ ኦ ኤስ ሀዋሳ” ጋር በመቀናጀት ላደረጉት ድጋፍ አመስግነው፤ ይህም የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

የአምብቾ ጎዴ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ሰለሞን ሎምቤቦ፤ የተደረገው ድጋፍ በትምህርት ቤቱ የነበረውን የቁሳቁስ ችግር በመቅረፍ የተማሪዎች ውጤትን ለማሻሻል አይነተኛ ሚና ያለው በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ዘጋቢ: አሚና ጀማል – ከሆሳዕና ጣቢያችን