በክልሉ የሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራት እና ዩኒየኖች ምርታቸውን የሚያስተዋውቁበትና የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበት ሁለተኛ ዙር ክልል አቀፋ ኤግዚቢሽንና ባዛር በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ከሰኔ 6 እስከ ሰኔ 9/2017 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል
ጉዳዩን አስመልክቶ በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ስሩር እና የክልሉ ህብረት ስራ ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጎዴቦ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
በሚካሄደው ኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ 30 የህብረት ስራ ማህበራት እና ዩኒየኖች እንደሚሳተፉና 45 የሰብል አይነቶች የሚቀርቡበት መሆኑ ተመላክቷል::
ክልሉ የበርካታ የግብርና ጸጋ ባለቤት መሆኑን ያነሱት አቶ ኡስማን ስሩር፤ እነዚህን ምርቶች ለማስተዋወቅ እና የገበያ ትስስር ለመፍጠር የኤግዚቢሽኑና ባዛሩ ፋይዳ የጎላ ነው ብለዋል::
ህብረት ስራ ማህበራት ለአርሶ አደሩ የገበያ ትስስር ከመፍጠርና የቁጠባ ባህልን ከማሳደግ ባለፈ የህብረተሰቡን ኑሮ ማሻሻል ላይ መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል አቶ ኡስማን::
በእለቱም በግብርና ዘርፍ ማቀነባበር ላይ ያሉ ማህበራት እና ዩኒየኖች እንደሚሳተፉ እና 45 የግብርና የሰብል አይነቶች እንደሚቀርቡ የተናገሩት ደግሞ የክልሉ የህብረት ስራ ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጎዴቦ ናቸው።
በሲምፖዚየሙና ባዛሩ ላይ 3 ሺህ አምስት መቶ ኩንታል በላይ ምርት፣ 16 ሺህ ሊትር ዘይት እንደሚቀርብ ያነሱት አቶ ተመስገን፤ ከስምንት ሺህ በላይ ሸማቾች ይጎበኛሉ ተብሉ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
ሁለተኛው ዙር ክልል አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛሩ የህብረት ሥራ ሚና ለዘጎች ብልጽግና በሚል መሪ ቃል ነው ከሰኔ 6 እስከ ሰኔ 9/2017 በሆሳዕና ከተማ የሚካሄደው።
ዘጋቢ፡ እፀገነት ፈለቀ

More Stories
በኮሬ ዞን የአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች መልሶ የማደራጀት ምክክር መድረክ ተካሄደ
በአጋር ድርጅቶች የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች የመንግስት የልማት ክፍተት በመሙላት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ
በሌማት ትሩፋት ከቤት ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን የምዕራብ አባያ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ