ቢሮው የክልሉን የመኸር እርሻ ልማት ስራዎች የ2016/17 የምርት ዘመን አፈጻጸምና የ2017/18 የምርት ዘመን ዕቅድ የንቅናቄ መድረክ በቦንጋ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።
ክልሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ ያለውን ዕምቅ አቅም ለመጠቀም በሰራው ስራ ምርትና ምርታማነት ከመጨመሩም ባሻገር የማሳ አጠቃቀም ዘይቤ ከፍ ማለቱን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ገልጸዋል።
በዚህም በዓምናው የመኸር አዝመራ በዋና ዋና ሰብሎች ከ3 መቶ 88 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳን በማልማት የማሳ ሽፋንን ከዕቅዱ አንጻር 99 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።
በዚህ መነሻነት የዘንድሮ የበልግ አዝመራ አፈጻጸምም የተሻለ መሆኑን የገለጹት አቶ ማስረሻ፤ በዚህም 3 መቶ 59 ሺህ ሄክታር ማሳን በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት ታቅዶ ከዕቅድ በላይ ማልማት እንደተቻለ ተናግረዋል።
ከዚህም 25 ሺህ ሄክታሩ በትራክተር የለማ ሲሆን 95 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያና 193 ሺህ ቶን ኮምፖስት ለግብዓትነት መዋሉንም ጠቅሰዋል።
ከዚህም አብዛኛው መሬት በክላስተር መልማቱን የገለጹት አቶ ማስረሻ፤ በዚህ መነሻነት በ2017/18 የመኸር አዝመራ በተሻለ መልኩ ለመስራት ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል።
በመሆኑም በዘንድሮ የመኸር አዝመራ እንደ ክልል በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ከ4 መቶ ሺህ ሄክታር በላይ ማሳን በማልማት ከ17 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግረዋል።
ለዚህም እርሻ 1 መቶ 26 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ለግብዓትነት እንደሚውልም ጠቅሰዋል።
ከዚህ ባሻገር በክልሉ የተጀመረው የሌማት ትሩፋት ስራ በወተት፣ በእንቁላል፣ በንብ ማነብና በአሳ ማስገር ውጤታማ መሻሻል እንደታየበትም ጠቁመዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ካለን የግብርና እምቅ አቅም አንጻር የቴክኖሎጂ ስርጸት፣ የተባይና የአረም ቁጥጥር ስራና የግብዓት ገንዘብን በወቅቱ ያለመሰብሰብን የመሳሰሉ ችግሮች አሁንም ለግብርናው ዘርፍ ዕድገት ማነቆ በመሆኑ በትኩረት መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል።
በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብርም ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ባላቸው ችግኞች እንደሚሸፈንም ጠቁመዋል አቶ ማስረሻ።
መድረኩን የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊና የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማንን ጨምሮ የክልል፣ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮችና የዘርፉ ባለሙያዎች እየተሳተፉበት ይገኛል።
ዘጋቢ፡ ታጋይ ገ/ሚካኤል – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
የወላይታ ዞን “ሁለንተናዊ የሴቶች ተሳትፎ ለጋራ ብልፅግና” በሚል ሀሳብ የተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ዞናዊ የውይይት መድረክ ተካሄደ
“ሀገሬን እገነባለሁ ኃላፊነቴንም እወጣለሁ”በሚል መሪ ቃል የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶች ክልል አቀፍ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል
የጉንችሬ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ ልማት በማፋጠን የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሻሻል ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ገለፀ