ሀዋሳ፡ ግንቦት 27/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ፈተናዎችን አልፎ ስኬት ማስመዝገብ እንደሚገባና የንግዱ ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ መነጋገር ያስፈልጋል ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ ገለጹ፡፡
ለሁለንተናዊ ብልጽግና የንግዱ ማህበረሰብ ሚና በሚል መሪ ሃሳብ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስተባባሪነት ክልል አቀፍ የንግዱ ማህበረሰብ የዉይይት መድረክ በቡታጅራ እየተካሄደ ነው።
በውይይት መድረኩ የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱን ጨምሮ የኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አባስ መሃመድ፣ ከክልሉ ሁሉም መዋቅሮች የተወከሉ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ተሳታፊ ሆነዋል።
የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት አቶ አንተነህ ፍቃዱ፤ ብልጽግናን ከንግዱ ማህበረሰብ ውጪ ማሳካት ስለማይቻል ተቀራርቦ መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ፈተናዎችን አልፎ ስኬት ማስመዝገብ እንደሚገባና የንግዱ ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ መነጋገር ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል።
የንግዱ ማህበረሰብ ሀብትና የስራ እድል በመፍጠር ባለሀብቱ በአካባቢው መጥቶ ኢንቨስት ማድረግ እንዳለበትና በክልሉ የኢንቨስትመንት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር መስራት ይጠበቅብናል ሲሉም ምክትል ርዕሰ መስተደድሩ ተናግረዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው በበኩላቸው፣ ክልሉ ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆንም ክልሉ የሚታወቅበት የንግድ ዘርፍ ማህበረሰብ የሚገኝበት ክልል ነው ብለዋል።
በመሆኑም እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር የንግዱ ዘርፍ ማህበረሰቡ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ መስተካከል የሚገባቸውን ጉዳዮች በጋራ ተወያይተንና መክረን የጋራ አቋም ለማያዝ ያስችላል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ ባለፉት 9 ወራት ለመሰብሰብ ከታቀደው 20 ቢሊዮን ብር ገቢ 14 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል ሲሉም ተናግረዋል።
እንደ ሀገር የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በመንግስት ድጎማ ከ6 ሚሊየን ሊትር በላይ ዘይትና ከ150 ሺህ ኩንታል በላይ ስኳር ለክልሉ ማህበረሰብ ማቅረብ ተችሏል ብለዋል።
በውይይት መድረኩ የብልጽግና ጉዟችንና የንግዱ ማህበረሰብ ሚናን በተመለከተ መነሻ ጽሁፍ እየቀረበ ሲሆን ውይይት ይደረግበታል።
ዘጋቢ፡ ወንድወሰን ሽመልስ

More Stories
በ6 ወራት ውስጥ ሊመዘበር የነበረ ከ156 ሚሊየን 560ሺህ ብር በላይ ማዳን መቻሉ ተገለጸ
የጉራጌ ክትፎ ባህልና እውቀትን በዩኒስኮ የሰው ልጆች ወካይ የማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተሰራ እንደሚገኝ የኢፌዲሪ ቅርስ ባለስልጣን ገለፀ
በክልሉ ያሉ ብሔረሰቦችን ባህል ወደፊት በማውጣት የአካባቢውን ሰላምና ልማት ለማስቀጠል በትኩረት መስራት እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳደር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ተናገሩ