በዞኑ ኩረጃን የሚፀየፍ ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ

የዞኑ ትምህርት መምሪያ በ2017 ዓ.ም የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍሎች ክልል አቀፍ ፈተና ዙሪያ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የምክክር መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።

በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የጉራጌ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ዓለማየሁ ገብረመስቀል እንዳሉት፤ በዞኑ ኩረጃን የሚፀየፍ በራሱ የሚተማመን ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ለማፍራት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።

የትምህርት ባለድርሻ አካላት በተለይም መምህራን፤ ተማሪዎች ተረጋግተው ያለምንም አይነት የኩረጃ እንቅስቃሴ ፈተናውን እንዲወስዱ ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ለዚህ ስኬታማነት በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በቂ መመሪያ እና አቅጣጫ መስጠት እንደሚገባቸው አመላክተዋል አቶ አለማየሁ።

የ2017 ዓ.ም የ6ኛ እና 8ኛ ክፍሎች ክልላዊ ፈተና በሰላም እንዲጠናቀቅ የዞኑ አስተዳደር አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማሪያም የ2017 ዓ.ም ክልል አቀፍ የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ፈተና ኦረንቴሽን በሰጡበት ወቅት የመድረኩ ዓላማ ፈተናው ሰላማዊ እና ከኩረጃ የፀዳ እንዲሁም ደህንነቱ ተጠብቆ እንዲካሄድ የሚያስችል መመሪያ በየደረጃው ለሚገኙ መዋቅሮች ለመዘርጋት ነው ብለዋል።

በመድረኩ የፈተናው ቅድመና ድህረ ጥንቃቄዎች ላይ ሰፊ ውይይት መደረጉን ያነሱት አቶ መብራቴ፤ ይህም ፈተናው በስኬት እንዲጠናቀቅ ጉልህ ፋይዳ ያበረክታል ነው ያሉት።

በዞኑ በ377 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 17 ሺህ 225 እንዲሁም በ328 ትምህርት ቤቶች 22 ሺህ 44 መደበኛ፣ የማታና የግል ተፈታኝ ተማሪዎች ፈተናውን ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል አቶ መብራቴ።

የፈተና ሂደቱን የሚቆጣጠሩ 1ሺህ 460 ባለሙያዎች በፈታኝነት፣ በሱፐርቫይዘርነት እና በጸጥታ አስከባሪነት እንዲሁም ፈተናውን የማስተባበር ስራ እንደሚያከናውኑም ጠቁመዋል የመምሪያው ኃላፊ።

ወቅቱ ዝናባማ በመሆኑ ተማሪዎች በአቅራቢያቸው ፈተናውን የሚወስዱበት ሁኔታ የማመቻቸት ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል።

በዞኑ የሚከናወነው ከኩረጃ የፀዳ የፈተና ስነስርዓት ሊያውኩ የሚችሉ እንደፈተና ተሰርቋል አሊያም ወጥቷል በሚል ተማሪዎችን ለማደናገር የሚሞክር ግለሰብ አሊያም ቡድን ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ በመጠቆም የትምህርት ማኅበረሰቡም ከመሰል ተግባራት ተማሪዎችን መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ሁሉም ተማሪዎች በፈተና ማእከላት ተገኝተው ኦረንቴሽን መውሰድ እንደሚጠበቅባቸው ያመላከቱት የመምሪያው ኃላፊው፤ የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ከሰኔ 3 አስከ 4/2017 ዓ.ም የሚሰጥ ሲሆን የ6ኛ ክፍል ደግሞ ከሰኔ 5 እስከ 6/2017 ዓ.ም እንደሚሰጥ ተማሪዎች ከወዲሁ አውቀው እንዲዘጋጁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የጉራጌ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ የህያ ሱልጣን እና የዞኑ ሚሊሻ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ገብሬ ተቋሞቻቸው ከፈተና ወረቀቱ ደህንነት እንዲሁም ተማሪዎች ፈተናውን በሰላም ጀምረው እስኪጨርሱ ድረስ በመድረኩ የተቀመጡ አቅጣጫዎች ተከትለው በየደረጃዉ ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተው ለመስራት መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉት በዞኑ በሚገኙ በሁሉም ወረዳና ከተማ አስተዳደሮች ወጥነት ያለው የፈተና አሰጣጥ ክትትልና ቁጥጥር እንዲኖር ለማስቻል ኦረንቴሽኑ በትክክለኛው ወቅት ለተገቢ ባለድርሻ አካላት ተሰጥቷል።

በዞኑ ካለፈው ዓመት የውጤት ስብራት ትምህርት ተወስዶ ከፍተኛ የትምህርት ጥራት ለማምጣት ጥረት ተደርጓል ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ ይህንን ጥረት ፍሬ እንዲያፈራ ተማሪዎቸ ተረጋግተው ከኩረጃ የጸዳ ፈተና እንዲወስዱ በቅንጀት እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።

በመድረኩ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማን ጨምሮ የወረዳ አስተዳዳሪዎችና የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ የሴክተር ሃላፊዎች ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፡ ሪድዋን ሰፋ – ከወልቂጤ ጣቢያችን