ሕዝበ ሙስሊሙ የኢድ-አልአደሃ አረፋ በዓልን ሲያከብር በሃይማኖቱ አስተምሮት መሠረት አቅመ ደካሞችን በመርዳትና ያለውን በማካፈል ሊሆን ይገባል – የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ኡስታዝ ሳዲቅ ወጌቦ

ሕዝበ ሙስሊሙ የኢድ-አልአደሃ አረፋ በዓልን ሲያከብር በሃይማኖቱ አስተምሮት መሠረት አቅመ ደካሞችን በመርዳትና ያለውን በማካፈል ሊሆን ይገባል – የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ኡስታዝ ሳዲቅ ወጌቦ

ሕዝበ ሙስሊሙ የኢድ-አልአደሃ አረፋ በዓልን ሲያከብር በሃይማኖቱ አስተምሮት መሠረት አቅመ ደካሞችን በመርዳትና ያለውን በማካፈል ሊሆን እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ኡስታዝ ሳዲቅ ወጌቦ አስታወቁ።

ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ለ1 ሺህ 446ኛው ዓመተ ሂጂራ የኢድ-አልአደሃ አረፋ በዓል እንኳን አደረሳችሁ ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ኡስታዝ ሳዱቅ ወጌቦ እንደተናገሩት፤ የአረፋ በዓል አላህ ነብዩ ኢብራሂምን ልጃቸውን እስማኤልን ለመስዋዕትነት እንዲያቀርቡ ያዘዛቸው ኢብራሂምም ሳያመነቱ ለፈጣሪ የነበራቸውን የእምነትና የፍቅር ጥግ በማሳየት ልጃቸውን ለመስዋዕትነት ሲያቀርቡ ፈጣሪም በምትኩ የበግ ሙክት አዘጋጅቶ መስዋዕት የተደረገበትን በማስታወስ ህዝበ ሙስሊሙ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች በድምቀት የሚያከብርበት በዓል ነው።

አረፋ አዳምና ሐዋ ከጃነት ወጥተው ለረዥም ጊዜ ተለያይተው ከሰነበቱ በኋላ በአራፋት ተራራ መገናኘታቸው የሚዘከርበት በዓል ነው ያሉት ዋና ፀሐፊው፤ ሙስሊሞች የመስዋዕት በዓሉን አረፋ እርድ በመፈጸም በጋራ ዱኣ በማድረግና ከፈጣሪ ምህረትን የሚያስገኙ በጎ ተግባራትን በማከናወን የምናከብርበት ነው ብለዋል።

በመሆኑም ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር በሃይማኖቱ አስተምህሮት መሠረት አቅመ ደካሞችን በመርዳት፣ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ያሉ ወገኖችን በመጠየቅ፣ በመተሳሰብና ያለውን በማካፈል ሊሆን እንደሚገባም ኡስታዝ ሳዲቅ አሳስበዋል።

የሀዲያ ዞን የሁለማዎች ጉባኤ ዋና ፀሐፊና የሶሮ ወረዳ ሻሪያ ፍርድ ቤት ዳኛ ኡስታዝ ሱልጣን ኡስማን እና የሆሳዕና ከተማ የእስልምና ጉዳይ መስጂድና አውቀፍ ዘርፍ ሀላፊ ሃጂ አብደላ ሀሰን በበኩላቸው፤ የኢድ-አልአደሃ አረፋ በዓል ከጾምና ፀሎት ሃይማኖታዊ ሥርዓት በኋላ የሚከናወንና በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው በዓል መሆኑን ተናግረዋል።

በመጨረሻም ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1 ሺህ 446ኛው የዓመቱ ሂጂረ ኢድ-አልአደሃ የአረፋ በዓል አደረሳችሁ በማለት በዓሉ የሠላምና የጤና እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።

ዘጋቢ: ሙሉነሽ ለማ – ከሆሳዕና ጣቢያችን