የዘንድሮው የአረፋ በዓልን ምክንያት በማድረግ ወደ ጉራጌ ዞን የሚገቡ እንግዶች በዓሉን በሰላም አክብረው እንዲመለሱ የተቀናጀ ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ተገለፀ

የዘንድሮው የአረፋ በዓልን ምክንያት በማድረግ ወደ ጉራጌ ዞን የሚገቡ እንግዶች በዓሉን በሰላም አክብረው እንዲመለሱ የተቀናጀ ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ተገለፀ

የጉራጌ ዞን ሠላምና ፀጥታ እና የዞኑ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያዎች ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በወልቂጤ ከተማ የውይይት መድረክ አካሂደዋል።

የዞኑ ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ሃላፊ አቶ ያህያ ሱልጣን በዚህ ወቅት እንዳሉት የአረፋ በዓልን ለማክበር ወደ ዞኑ የሚመጡ እንግዶች የፀጥታ ችግር እንዳይገጥማቸው የፀጥታ አካላት በመናበብ መስራት ይጠበቅባቸዋል።

ኬላዎችም እንግዶችን ከመቀበል ባሻገር ለፍተሻ በሚል እንግልት መፍጠር እንደሌለባቸው አቅጣጫ መቀመጡን በመጠቆም ይሁን እንጂ ለደህንነት ስጋት የሆኑ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ ጉዳዩን ማጣራት እንደሚገባ ነው አቶ ያህያ የተናገሩት።

ሌብነትና የወንጀል ድርጊቶች እንዳይፈፀሙ ገበያና ባንኮች ያሉባቸው አካባቢዎች የተለየ ጥንቃቄ ስለሚያስፈልግ የፀጥታ ሀይሉ ትኩረት ሊሠጥ እንደሚገባ አስረድተዋል።

የጉራጌ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ሃላፊ ወ/ሮ ትብለጥ እስጢፋኖስ በበኩላቸው በዓሉን ለማክበር ወደ ዞኑ የሚገቡ እንግዶች በሠላም ገብተው በዓሉን አክብረው እስኪመለሱ የተቀናጀ ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ጠቅልል አባድየ እና አስቻለው ገብሬ በሠጡት አስተያየት ለበዓሉ የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል የቅድመ ዝግጅት ስራ በመስራት ላይ መሆናቸው ገልፀዋል።

እንግዶች ለበዓሉ ሲገቡም ሆነ ሲወጡ ችግር እንዳይገጥማቸው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በቂ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናቸው ተናግረዋል።

እንግዶቹ ወደ ወልቂጤ ከተማ ሲገቡ ለመቀበልና ሲወጡም ለመሸኘት መዘጋጀታቸውም አንስተዋል።

ዘጋቢ ፡ እቴነሽ ቲሬቦ-ከወልቂጤ ጣቢያችን