የጤና ባለሙያዎች የሰውን ሕይወት ከመታደግ አንጻር ከፍተኛ ኃላፊነት የሚጠበቅባቸው በመሆኑ ከመንግሥትና ከሕዝብ የተሰጣቸውን ኃላፊት በትጋትና በታማኝነት መወጣት ይኖርባቸዋል – ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

የጤና ባለሙያዎች የሰውን ሕይወት ከመታደግ አንጻር ከፍተኛ ኃላፊነት የሚጠበቅባቸው በመሆኑ ከመንግሥትና ከሕዝብ የተሰጣቸውን ኃላፊት በትጋትና በታማኝነት መወጣት ይኖርባቸዋል – ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

የጤና ባለሙያዎች የሰውን ሕይወት ከመታደግ አንጻር ከፍተኛ ኃላፊነት የሚጠበቅባቸው በመሆኑ ከመንግሥትና ከሕዝብ የተሰጣቸውን ኃላፊት በትጋትና በታማኝነት መወጣት እንዳለባው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አሳስቡ።

“የጤና ዘርፍ አርበኝነት፤ ለሀገር ዕድገት” በሚል መሪ ቃል ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ክልል አቀፍ ማጠቃለያ የውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።

በጤና ባለሙያዎች በኩል ችግሮችን በመቋቋም ለማህበረሰቡ እየተደረገ ስላለው ቅንነት ለተሞላው አገልግሎታቸው ምስጋና ይገባቸዋል ያሉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር፤ ሀገራዊና ወገናዊ የሆነ የዜግነት ግዴታችውን በተለመደው ሁኔታ እየተወጡ መሆናቸውም ተናግረዋል፡፡

በየተቋማቱ የሚታዩ ጉድለቶችንና ችግሮችን መንግስት ደረጃ በደረጃ እንደሚፈታ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ ገንቢና ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።

የጤና ተቋማቱን የሚመሩ ቦርዶች በየደረጃው ባሉት መዋቅሮች መኖራቸውን ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ከህግ ማዕቀፎችና ከተለያዩ አገልግሎት አሰጣጥ አኳያ የሚታዩ የሥራ ሁኔታዎች በተቀመጠው የአሰራር ሂደት ይፈታሉ ብለዋል፡፡

አንዳንድ ችግሮች ከዚህ ቀደም ተያይዞ ከመጡት ዕዳ ጫናዎች የተነሳ ለሚነሱ ጥያቄዎች የምላሽ መዘግየት መኖሩን የገለጹት ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ፤ እንደጥያቄያቸው ሁኔታ ከታችኛው መዋቅር ጋር በመነጋገው የመኖሪያ ቤትና ተያያዥ ችግሮች ተገቢ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አስረድተዋል፡፡

መንግስት የጤና ተቋማትንና የባለሙያውን ችግር ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ እየመራ መሆኑን ያብራሩት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም፤ በውይይትና በምክክር ችግሮችን እየፈታን የሕዝብን እርካታ ከማረጋገጥ አኳያ በመቀናጀት የጤናውን ተቋም ውጤታማ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።

ከጤና ባለሙያዎች የአገልግሎትና የመብት ጥያቄዎች፣ የጥቅማ ጥቅም ጉዳይ፣ አንዳንድ ጤና ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ተልዕኮ በአግባቡ መወጣት እንዳይችሉ የግብዓት እጥረቶችና የትምህርት ማሻሻያዎች በሚመለከታቸው አካላት ምላሽ እንዲያገኙ ጠይቀዋል፡፡

የለውጡን ሂደት በጤና ባለሙያው ትከሻ ተረማምደው ለማደናቀፍ የተደረጉ ጥረቶች በእናንተ አርቆ አሳቢነት፣ አስተውሎትና በጎ ምላሽ የአገልግሎት አሰጣጡ ሳይደናቀፍ በመቀጠሉ ምስጋና ይገባችኋል ያሉት ደግሞ የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን ናቸው፡፡

የጤና ባለሙያው ያነሳው ጥያቄ ተገቢነት ያለው በመሆኑ መንግስት ደረጃ በደረጃ የሚፈታ መሆኑን የገለጹት አቶ ፍቅሬ፤ ተቋሙን አግባብነት ባለው ሁኔታ በእንክብካቤ በመያዝ ትልቅ የሆነውን የሙያ ተልዕኮአቸውን በብቃትና በታማኝነት መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

“የጤና ዘርፍ አርበኝነት፤ ለሀገር ዕድገት” በሚል መሪ ቃል ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ክልል አቀፍ ማጠቃለያ የውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ የተደረገ ሲሆን በውይይት መድረኩ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ማስረሻ በላቸው፣ ሌሎች ከፍተኛ የክልሉ አመራሮችና ከተለያዩ የጤና መዋቅሮች የተውጣጡ ባለሙያዎችና ሰራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ዘጋቢ፡ መለሠ ገብሬ – ከቦንጋ ጣቢያችን