የሴቶች አረፋን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን በጉራጌ ዞን እኖር ወረዳ ያነጋገርናቸው የእስልምና እምነት ተከታይ እናቶች ተናገሩ

የሴቶች አረፋን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን በጉራጌ ዞን እኖር ወረዳ ያነጋገርናቸው የእስልምና እምነት ተከታይ እናቶች ተናገሩ

ሃይማኖታዊ በአላት ይዘታቸውን ሳይለቁ ባህላዊ ፋይዳቸውንም በመረዳት ለትውልድ እንዲሸጋገሩ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ የእኖር ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የአረፋ በአል በጉራጌዎች ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባለፈ ብዙ መልኮች አሉት።

ለዚህም ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ዝግጅቶች በዓሉ ከመድረሱ ቀደም ብለው ባሉት ወራቶች ውስጥ ይጠናቀቃሉ፡፡

በዚህ መሰረትም እናቶች ለበዓሉ የሚሆን በተለይም እለቱ (የሴቶች አረፋ ማለት) የዋናው በአል ዋዜማ እንደመሆኑ መጠን የሴቶች አረፋን በተለየ አኳኋን ይጠበቡበታል፤ ከወንዶቹ (ከአባወራው) የመፎካከርና በልጦ የመገኘት በሚመስልም መንገድ።

ቆጮ ከመፋቅ እስከ መጋገር ድረስ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ቅቤ በማዘጋጀት፣ ሚጥሚጣ በመውቀጥ ደፋ ቀና ሲሉ ይሰነባብታሉ፡፡ እለቱንም ከልጆቻቸው ባልተናነሰ መልኩ በጉጉት ይጠብቁታል፡፡ ምክንያቱም ባለበሌለ አቅማቸው በፈቀደው ሁሉ ለወራት ሲዘገጃጁ የከራረሙበትን ውጤቱ በአሉ ላሰባሰበው ቤተሰብና ወዳጅ ዘመድ ሊያቋዱሱ ነውና።

ምንም እንኳን ከቅድመ ዝግጅት እስከ ለተ በአሉ ያለው ሂደት አድካሚ ቢሆንም ቅሉ ይህ ግን ለአዘጋጆቹ እናቶች ስሜቱ የድካም ሳይሆን ከደስታም በላይ ሆኖ ይሰማቸዋል። ምክንያቱም ይህ ለት በተለያዩ ምክንያቶች ተራርቀው የነበሩ ልጆቻቸው ተሰባስበው የሚገናኙበትም ነውና።

የጉራጌ እናቶች መች ይህን ብቻ በአረፋ በአል የሚጠበቅባቸው ብዙ ነው፡፡ ከሴት ልጆቻቸው ጋር ደግሞ የመኖሪያ ቤቶችን በማስዋብ፣ የመመገቢያ ቁሶችን በማፅዳት፣ የቤተሰቡን አልባሳት ሁሉ በማጠብና ሌሎች ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ቅድመ መሰናዶዎችን በማሟላት ስራም ይጠመዳሉ፡፡

የሴቶች አረፋ ዕለት ሴቶች የጎመን ክትፎ እና ዝማሙጃት በማዘጋጀት እንዲሁም የቂቤ ቡና በማፍላት ቤተ ዘመድና ጎረቤት በመጥራት በፍቅር የሚገባበዙበትና የሚደሰቱበት በተለይም ለሴቶች የአረፋ ዋዜማው ልዩ ዕለት ነው፡፡

ወ/ሮ ፈትያ ዮሃንስና ወ/ሮ ሰሚራ ዘርጋ ካነጋገርናቸው የወረዳው ነዋሪዎች መካከል ናቸው።

ታዲያ እናቶቹ በሰጡን አስተያየት እንደወትሮው ሁሉ ለ1446ኛው ኢድ-አልአድሃ በአል በተለይም ለሴቶች አረፋ በአል እለት የሚሆነው ሁሉ ዝግጅታቸው አጠናቀው እለቱን በጉጉት እየተጠባበቁት እንዳሉም ነግረውናል።

ከወራት በፊት የቂቤ እቁብ (ውጆ) በመሰብሰብ ለበአሉ የሚሆን የቂቤ መጠን ማዘጋጀታቸውና ቆጮም ቢሆን የተመረጡ እንሰቶች አስቀድመው በመፋቅ የቆጮ አጠባውን ጨምሮ የባህላዊ መመገቢያ ቁሳቁሶችን ሁሉ በተጠንቀቅ አዘገጃጅተው ማጠናቀቃቸውንም አብራርተውልናል ወ/ሮ ፈትያ ዮሃንስና ወ/ሮ ሰሚራ ዘርጋ።

እናቶቹ በመጨረሻም በጉጉት የሚጠብቋቸውን እንግዶቻቸው በሰላም እንዲደርሱላቸው ዱአ እያደረጉላቸው እንዳሉና ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክትም አስተላልፈዋል እናቶቹ።

ወ/ሮ ጨዋነሽ ኢማም የእኖር ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ሃላፊ ናቸው።

የአረፋ በአል እንደጉራጌ ብሄረሰብ ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባሻገር ባህላዊ በሆነ መልኩም በተለየ ድምቀት እንደሚከበር አንስተው በእኖር ወረዳም በተመሳሳይ በየአመቱ ባማረ ሁኔታ የሚከበር ነው ብለዋል።

በመሆኑም በአሉ ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባለፈም በውስጡ በርካታ ባህላዊ እሴት ያለው በመሆኑ ይህን ይበልጥ ለማጎልበት ጽ/ቤቱ በትኩረት እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት።

የአረፋ በአል በውስጡ ከያዛቸው ኩነቶች መካከል በዋዜማው ደሞቆ የሚያመሸው የሴቶች አረፋ በአል አንዱ መሆኑን የተናገሩት ወ/ሮ ጨዋነሽ፤ ይህም የማህበረሰቡ መገለጫ በመሆኑ ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ሳይቃረን ባህላዊ ኩነቱን በላቀ ደረጃ ለማስቀጠልና ለትውልድ እንዲሸጋገር በተገቢው እየተሰራበት ይገኛል ሲሉም ገልፀዋል።

በወረዳው የአረፋ በአል አከባበርን ጨምሮ ሌሎች የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ በርካታ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች መኖራቸውን የገለፁት ሃላፊዋ፤ ይህም ወደ ወረዳው ለሚመጡ እንግዶችና ለተወላጁም በስፋት ለማስተዋወቅ በሚያግዝ መልኩ ብሮሸሮችንና ባነሮችን የማዘጋጀት ስራም ተሰርቷል ብለዋል።

የወረዳው ብሎም የመላው ጉራጌ ህዝብ መገለጫ የሆኑት የመስቀልና የአረፋ በአላት ሃይማኖታዊ ይዘታቸውን እንደጠበቁ ባህላዊ ክዋኔዎቻቸውንም ለቀጣይ ትውልድ ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት ሁሉም ሊያግዝ፣ ባህሉን ሊጠብቅና ሊንከባከብ ይገባልም ብለዋል።

በመጨረሻም ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ያስተላለፉት ወ/ሮ ጨዋነሽ፤ የአካባቢው ተወላጅን ጨምሮ ለበአል ወደ ወረዳው የሚመጡ እንግዶች በወረዳው የሚገኙ የተለያዩ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ እንዲሁም ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን እንዲጎበኙ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡ ሚፍታ ጀማል – ከወልቂጤ ጣቢያችን