በተለያዩ መስኮች የሰለጠኑ እጩ ምሩቃንን ወደስራ ለማሰማራት ከቀጣሪ ተቋማት ጋር ትስስር መፍጠር እንደሚገባ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ
ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን እጩ ተመራቂዎች ከቀጣሪ ድርጅቶች የሚያገናኝ የስራ አውደ ርዕይ እያካሄደ ነው።
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ፋሪስ ደሊል በእንኳን ደህና መጣችሁ የመክፈቻ ንግግራቸው፤ በዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ የሙያና የስራ አውደ ርዕይ ሲዘጋጅ የ2017 እጩ ተመራቂዎች የወደፊት የስራ እድልን ለማመቻቸት እና ድርጅቶችም የሰለጠነ የሰው ሀይል በቀላሉ እንዲያገኙ በማለም ነው ብለዋል።
የአገራችንን የትምህርት ጥራት ስብራት ለመጠገን በመንግስት በተጀመረው የዘርፉ የለውጥ ስራዎች እጩ የተግባር ተኮር ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የሆነው ዩኒቨርሲቲው፤ በ2022 በአገራችን ከሚገኙ ተግባር ተኮር ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች ቀዳሚ የመሆን ራዕይ ሰንቆ እየተጋ ይገኛል ነው ያሉት።
ዩኒቨርሲቲው ከ2004 ጀምሮ ተማሪዎችን በመቀበል በርካታ የሰለጠነ ዜጋ ለአገር ያበረከተ ሲሆን ምሩቃን በቀጥታ ከቀጣሪ ተቋማት ጋር እንዲገናኙ ማድረግ ከሚፈጥርላቸው የስራ እድል በተጨማሪ ድርጅቶችም የሚፈልጓቸውን ምሩቃን በበቂ ሁኔታ እዲያገኙ ያግዛቸዋል ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶክተር ሀብቴ ዱላ፤ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቹን በእውቀትና በክህሎት ከማብቃት ባሻገር ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር ለማገናኘት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
እንደ አገር የሚፈለገውን ብቁ ዜጋ ለማፍራት በርካታ ስራዎች እየሰራ ነው ያሉት ዶክተር ሀብቴ፤ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ እጩ ምሩቃንና አሰሪ ተቋማትን ለማገናኘት ዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀው የሙያና የስራ አውደርዕይ እድል ምሩቃን በሰለጠኑበት የሙያ መስክ በአግባቡ እንዲጠቀሙበት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በስነ-ስርዓቱ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ እጩ ምሩቃንን ከቀጣሪ ድርጅት ጋር ለማገናኘት ያደረገው ጥረት አርዓያ የሚሆን ተግባር ነው ብለዋል።
እንደ አገር የተጀመረው የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በጥናትና ምርምር የታነፀ ዜጋ የሚገኘው ዩኒቨርሲቲ በመሆኑ ምሩቃንን ከቀጣሪ ድርጅቶች የማገናኘት ስራው መጠናከር አለበት ሲሉ አስረድተዋል።
አውደ ርዕዩ እጩ ምሩቃን በሰለጠኑበት ዘርፍ የስራ እድል ከማመቻቸት ባሻገር ቀጣሪ ተቋማት የሚፈልጉትን የሰለጠነ የሰው ሀይል እንዲያገኙ አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።
የስራ አውደ ርዕይ ስነ-ስርዓቱ በነገው እለትም የሚቀጥል ሲሆን በርካታ የመንግስት እና የግል ድርጅቶች ምርትና አገልግታቸውን በማስተዋወቅ እተሳተፉ ይገኛሉ።
ዘጋቢ፡ አዱኛ ትዛዙ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በ2017 የግብር ወቅት ከደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱ ተገለጸ
የህብረተሰቡን ጤና ለማጎልበት የዘርፉን ተግባራት በተገቢው ለማሳካት ከምንጊዜውም በተሻለ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ
የህዝቡን የልማት ፍላጎቶች ለማሟላትና መንግስታዊ አገልግሎቶችን በተገቢው ለመስጠት የውስጥ ገቢ ግብርን አማጦ ለመሰብሰብ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ተገለጸ