“የጤና ዘርፍ አርበኝነት፤ ለሀገር ዕድገት” በሚል መሪ ቃል ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ክልል አቀፍ ማጠቃለያ የውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተደረገ ይገኛል

“የጤና ዘርፍ አርበኝነት፤ ለሀገር ዕድገት” በሚል መሪ ቃል ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ክልል አቀፍ ማጠቃለያ የውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተደረገ ይገኛል

በመድረኩ ላይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ እንደገለጹት፤ የጤና ሙያ የሰውን ልጅ ሕይወት ከመታደግ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው ሙያ በመሆኑ የሙያው ባለቤት መሆን በራሱ መታደል ነው።

የሚከሰቱ ችግሮችን በመመካከርና በመወያየት ደረጃ በደረጃ መፍታት ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የጤና ባለሙያ የጸረ ሰላም ኃይሎች መነገጃ ሳይሆን የሙያውን ሥነ-ምግባር በመላበስ ሰብዓዊ አገልግሎቱን ለማህበረሰቡ ማድረስ ይገባዋል ብለዋል።

እስካሁን ባለው ሂደት ችግሮችን በመቋቋም ለማህበረሰቡ እያደረጋችሁት ላለው ቅን አገልግሎት ምስጋና ይገባችኋል ብለዋል።

ይህም ሀገራዊ እና ወገናዊ የሆነ የዜግነት ግዴታ በመሆኑ የተለመደውን ተልእኮአችሁን መወጣት አለባችሁ በማለት አሳስበው፤ በየተቋማቱ የሚታዩ ጉድለቶች በየደረጃው እንደሚፈቱ ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

የመወያያ ሰነድ በክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም ቀርቧል።

በውይይቱ ወቅትም የተለያዩ ችግሮች፣ ክፍተቶች እና ጉድለቶች ተነስተው ውይይት የተደረገ ቢሆንም እንደክልል ሊስተካከሉ የሚገባቸውን በመለየት የጋራ አቅጣጫ በመያዝ በክልሉ አቅም ለመሥራትና ከዚህ በላይ የሆኑት ደግሞ በሚቀጥለው አካል መፈታት የሚችሉ መሆኑን ነው አቶ ኢብራሂም የገለጹት።

መንግስት የጤና ተቋማትንና የባለሙያውን ችግር ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ እየመራ ያለበት ሂደት ስላለ በውይይትና በምክክር ችግሮችን እየፈታን እንደጤና ባለሙያ የሕዝብን እርካታ ከማረጋገጥ አኳያ ተቀናጅተን በመከወን የጤናውን ዘርፍ ውጤታማ ማድረግ አለብን በማለት አቶ ኢብራሂም አሳስዋሉ።

በቀረበው ሰነድ ዙሪያ ከተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ አካላት የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች እየቀረቡ ነው።

ዘጋቢ፡ መለሠ ገብሬ – ከቦንጋ ጣቢያችን