ወንጀልን የመከላከል መርህን መሠረት በማድረግ የሕብረተሰቡን ሠላምና ደህንነት ማስጠበቅ ይገባል – የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ
ወንጀልን የመከላከል መርህን መሠረት በማድረግ የሕብረተሰቡን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የሚሊሻ አባላት ከፀጥታ አካላት ጋር ሊሠሩ እንደሚገባ የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ ገለፁ።
“በጀግነት መጠበቅ በሰብዓዊነት ማገልገል” በሚል መሪ ቃል በዞኑ የሐመር ወረዳ ሚሊሻ ጽህፈት ቤት 2 መቶ 59 የሚሊሻ አባላትን አሰልጥኖ አስመርቋል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ተገኝተው መልክት ያስተላለፉት የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ፤ ወንጀልን የመከላከል መርህን በመከተል የሕብረተሰቡን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ተመራቂ ሚሊሻ አባላት ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እንዲሠሩ አሳስበዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ጎላ ጎዳቦ በበኩላቸው፤ ተመራቂዎቹ የማህበረሰቡንና የአካባቢውን ዘላቂ ሠላም ለማስጠበቅ ከመንግሥት ጎን በመቆም ወንጀል የመከላከል ሥራውን በኃላፊነት እንዲወጡ የሥራ መመሪያም ሰጥተዋል።
የሐመር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሣሙኤል ጋርሾ እንደገለፁት፤ የእድገትና የብልፅግና ዕቅዶችን ለማሳካትና የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ዘላቂ ሠላምና ልማትን ለማረጋገጥ የሚሊሻ አባላት ምረቃ ተጨማሪ አቅም መፍጠሩን አስረድተዋል።
የሐመር ወረዳ ሠላምና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡቲና አሪ እና አሰልጣኝ ኮንስታብል ቢንያም ዴሬ በጋራ እንደገለፁት፤ ከ34 ቀበሌያት የተውጣጡ 2 መቶ 59 የሚሊሻ አባላት መሠረታዊ የውትድርና ዕውቀትና ክህሎት ስልጠና አግኝተው ለምረቃ በቅተዋል።
ከሕብረተሰቡና ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን አካባቢያቸውን በተሻለ ደረጃ መጠበቅ የሚያስችል ዕውቀት ማግኘታቸውን ሰልጣኝ ምሩቃን ተናግረዋል።
ስልጠናው በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትና ሰልጣኞች የምስጋናና የዕውቅና ሰርተፊኬት ተሰጥቷቸዋል።
ዘጋቢ፡ ተመስገን አሰፋ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
የሰራተኞች የገንዘብ ቁጠባ እና ብድር ኅብረት ሥራ ማህበር ብዙዎችን የቤት ባለቤት ማድረጉ ተገለጸ
በሁሉም ዘርፎች እንደሀገር አመርቂ ውጤቶች እየተዘመገቡ ነው – የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች
የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስርዓትን በማዘመን የመረጃ ታማኝነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ