ምርጥ ዘሮችንና የግብርና ግብዓቶችን በማቅረብ ሀገሪቱ የያዘችውን በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት የበኩሉን እንደሚወጣ ማዕከሉ ገለጸ

ሀዋሳ፡ ግንቦት 24/2017 ዓ.ም (ደሬቴደድ) የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ቦንጋ ቅርንጫፍ ማዕከል የተለያዩ ደረጃ ያላቸውን ምርጥ ዘሮችንና የግብርና ግብዓቶችን በማቅረብ ሀገሪቱ የያዘችውን በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት የበኩሉን እንደሚወጣ ገለጸ፡፡

ማዕከሉ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በምርጥ ዘርና በግብርና ምርቶች ግብዓት አቅርቦት ዙሪያ ምክክር አካሂዷል፡፡

የግብርና ኮርፖሬሽን ከዚህ ቀደም በተናጠል ይሰጥ የነበሩትን አገልግሎቶች በአንድ መስኮት ለመስጠት እንዲያስችለው በአዋጅ ቁጥር 368/2008 የተቋቋመ ሲሆን ተቋሙ ከመሬት ዝግጅት እስከ ጎተራ የሚለውን መርህ ተግባራዊ በማድረግ የግብርና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ የሚረዱ ጥራት ያላቸው የሰብል ዘሮችን፣ የግብርና ግባቶችንና የእርሻ መሳሪያዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ድርሻውን እየተወጣ ነው ተብሏል፡፡

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ምክትልና የግብርና ግብዓትና ገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አስራት አሰፋ እንዳሉት፤ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የምርጥ ዘር ዝግጅተና በግብርና ግብዓት አቅርቦት ዙሪያ በርካታ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡

በምርጥ ዘር ዝግጅትና አቅርቦት ዙሪያ የተሰማሩ የዘር አባዢ አካላት እንደሀገር የተጣለባቸውን ኃላፊነት በትጋትና በታመኝነት እንዲወጡ አቶ አስራት አሰፋ አሳስበዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም የቦንጋ ቅርንጫፍ ማእከል ሥራ አስኪያጅ አቶ አስረስ አስፋው፣ የቦንጋ ዘር ጥራት ቁጥጥር ምርምር ማዕከል ባለሙያ አቶ ሲሳይ ታደሰ እና ሌሎች ባለሙያዎች በተቋሙ የሥራ እንቅስቃሴና በዘር አቅርቦት ዙሪያ የተዘጋጀውን ሰነድ አቅርበው ውይይት ተደርጓል፡፡

ከዘር አባዢዎች መካከል አቶ ክፍሌ ታደሰ እና ሌሎችም እንደገለጹት፤ መንግስት ተቋሙን በማቋቋሙ ከዚህ ቀደም ምርጥ ዘርና የግብርና ግብዓቶችን ለማግኘት ሲባል ይደርስ ከነበረው እንግልትና ውጣውረድ እንዳሳረፋቸው ገልጸው አሁን ባለው ሁኔታ የግብርና ሥራ በሰው ጉልበት የማይቻል በመሆኑ የገንዘብ ብድርና የማሽን አቅርቦት እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ምርጥ ዘርና የግብርና ግብዓቶችን በማቅረብ ሀገሪቱ የያዘችውን በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት የድርሻውን እንደሚወጣም ተገልጿል፡፡

ከተለያዩ አካላት ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ በኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና መ/ቤት የምርጥ ዘር ዘርፍ ከፍተኛ የዘር ምርት ባለሙያ የሆኑት አቶ አዳነ ኃይሌ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ምክትልና የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ መላኩ፣ የቦንጋ ዘር ጥራት ቁጥጥር ማዕከል ኃላፊ አቶ ተፈሪ ወ/ሚካኤል፣ የምርጥ ዘር አባዥ ድርጅት ተወካዮችና የተለያዩ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ዘጋቢ፡ መለሰ ገብሬ – ከቦንጋ ጣቢያችን