በጉራጌ ዞን ጌታ ወረዳ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በመንግስትና በህብረተሰብ ተሳትፎ የተገነቡ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች የምረቃ ስነ ስርዓት ተካሄዷል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት፤ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በመንግስትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተገነቡ የተለያዩ መሰረተ ልማት ስራዎች ተጠናቀው ለምረቃ መብቃታቸው በዞን ደረጃ በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው።
በዕለቱም ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ለሚገነባው የጉራጌን ባህላዊ እሴት አሟልቶ የያዘ ባህላዊ አዳራሽ ግንባታ መሰረተ ድንጋይ ሰነ ስርዓት መከናወኑን የገለፁት አቶ ላጫ በአጭር ጊዜ በጥራት ገንብቶ ለማጠናቀቅ የሁሉም ተሳትፎ እንዲጠናከር መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በዞኑ በትምህርት ልማት ስራ ህዝቡንና ባለሀብቱን በማሳተፍ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት ውጤታማ ናቸው ያሉት አቶ ላጫ በቀጣይ የትምህርት ዘመን ምዴል አዳሪ ትምህርት ቤት ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን ገልፀዋል።
ዋና አስተዳዳሪው አክለውም በ2018 ዓ.ም የስራ ዘመን በዞኑ ያሉ ቀበሌ መዋቅሮችን ከዋና መንገድ የሚያስተሳስር የመንገድ ልማት ስራ ይከናወናል ነው ያሉት።
የህብረተሰቡን የመሰረተ ልማት ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የህብረተሰቡና ባለሀብቱ ተሳትፎ ከመቼውም ጊዜ በላይ ማጠናከር ይገባል ሲሉ አቶ ላጫ ተናግረዋል።
የጌታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ በህሩ ኽይረዲን በበኩላቸው፤ በወረዳው በበጀት ዓመቱ በተለያዩ ቀበሌያት ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የ40 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ በመንግስትና በህብረተሰብ ተሳትፎ መከናወኑን ተናግረዋል።
በወረዳው በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታቸው የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን በመጨረስና አዳዲስ የመሰረተ ልማት ሰራዎችን በማጠናቀቅ የከተማውን ደረጃ ለማሻሻል እየተሰራ ነው ብለዋል አቶ በህሩ።
እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለፃ ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ በመንግስትና ህብረተሰብ ተሳትፎ በዛሬው ዕለት ተጠናቆ ለምረቃት የበቃው ባለ ሁለት ወለል አስተዳደር ህንፃ፣ የጌጠኛ የድንጋይ ንጣፍ መንገድና መሠል የልማት ሰራዎች ተጠቃሽ ናቸው።
የወረዳው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት፤ ከዚህ ቀደም መንገድ በአካባቢያቸው ባለመኖሩ ይቸገሩ እንደነበር አውስተው አሁን ላይ መንገድን ጨምሮ ሌሎች መሠረተ ልማቶች በመገንባታቸው ችግራቸው መፈታቱን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በዚህ ዓመት በአካባቢያቸው የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍና የውሃ መውራጃ ቱቦ በመሰራቱ ችግራቸው መፈታቱንና በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል።
በወረዳው የተጀመሩ የመሠረተ ልማት እና አዳዲስ የሚጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ ገልፀዋል።
በምረቃ ስነሥርዓቱ ላይ ለፕሮጀክቶቹ ስኬታማነት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
ዘጋቢ፡ ተዘራ በቀለ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎችን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሥራ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ገለጹ
የእናቶችንና ጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለፀ
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መስተዳደር (ዶ/ር ) እንዳሻው ጣሰው በተገኙበት በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ምርቃትና የመሰረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ-ስረዓት እየተካሄደ ይገኛል