ዩኒቨርሲቲዉ የጉራጊኛ ቋንቋ፣ ባህል እና ሀገር በቀል እዉቀትን ማልማት ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና ለሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች እና አመራሮች ሰጥቷል።
ስልጠናዉን በንግግር ያስጀመሩት የዩኒቨርሲቲዉ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሀብቴ ዱላ፤ ኢትዮጵያ በአህጉርም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቅበት የበርካታ እሴቶች ባለቤት ናት ብለዋል።
በመሆኑም እነዚህ እሴቶች ቀጣይነት እንዲኖራቸዉ የአሁኑ ትዉልድ ትልቅ ሀላፊነት እንዳለበትም አመላክተዋል።
ሚዲያዎች በህብረተሰቡ ላይ ትልቅ ተጽእኖ የመፍጠር አቅም አላቸዉ ያሉት ስልጠናዉን የሰጡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ እና ስነ ሰብ ኮሌጅ የሶሻል አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር አራጌ ይመር ናቸዉ።
በመሆኑም የሚዲያ ባለሙያዎች በቋንቋ እና ባህል ላይ ያገኙትን መልሰዉ መንገር ሳይሆን ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ መስራት ይጠበቅባቸዋልም ነው ያሉት።
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ፣ ባህልና ሃገር በቀል እውቀቶች ልማት ማእከል ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ካሚል ኑረዲን በበኩላቸው፤ የጉራጊኛ ቋንቋ እንዲበለፅግ፣ አካባቢን እንዲያስተዋውቅና አለምአቀፋዊ እውቅናን እንዲያገኝ ሚዲያና የሚዲያ አካላት ፈር ቀዳጅ በመሆናቸው ይህን ታሳቢ በማድረግ ዩኒቨርሲቲው ጅምር ተግባሮችን እያከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የስልጠናው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፤ የጉራጊኛ ቋንቋ የሚዲያ ቋንቋ ሆኖ እንዲያገለግል እየተደረገ ያለውን በማጠናከር በቀጣይ ቋንቋውን ይበልጥ ለማልማት በትኩረት መሰራት አለበትም ብለዋል።
በስልጠናው መድረክ የጉራጊኛ ቋንቋ ፊደላት፣ መማሪያ፣ ማስተማሪያና መፃፊያ መተግበሪያ ለሰልጣኞች ትውውቅ የተደረገ ሲሆን የዘዬዎች አጠቃቀምም የልምድ ልውውጥ ተደርጓል።
በዚህ ለሁለት ቀናት በተሰጠው ስልጠና ላይ በጉራጊኛ ቋንቋ የሚሰሩ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች እና አመራሮች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፡ ረድኤት እግዜሩ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
በኮሬ ዞን የአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች መልሶ የማደራጀት ምክክር መድረክ ተካሄደ
በአጋር ድርጅቶች የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች የመንግስት የልማት ክፍተት በመሙላት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ
በሌማት ትሩፋት ከቤት ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን የምዕራብ አባያ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ