የመምህራንን ሙያ ብቃት ምዘና በማካሄድ ለትምህርት ጥራት መጠበቅ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን የሸካ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ

የሸካ ዞን ትምህርት መምሪያ የመምህራን ሙያ ብቃት ምዘና በማሻ ማዕከል አካሂዷል።

የሸካ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን አለሙ፤ እንደ ሀገር ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀው የመምህራን ሙያ ብቃት ምዘና ማካሄድ የዚሁ ተልዕኮ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

በሸካ ዞን በአጠቃላይ ለ373 መምህራን፣ ርዕሰ መምህራንና ሱፐርቫይዘሮች በተለያዩ መፈተኛ ጣቢያዎች እየተሰጠ መሆኑን ገልፀው በማሻ ማዕከል ደግሞ ለ151 ተፈታኞች መሰጠቱን ጠቁመዋል አቶ መስፍን።

የመምህራን ብቃት ምዘናውን መሠረት በማድረግ በምዘናው ብቁ የሆኑ መምህራንን በመለየት እና ምዘናውን ለተከታታይ 3 ዙር ተፈትነው ከ70 በመቶ በላይ ማምጣት ላልቻሉት የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚሰጥም ጠቁመዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ የትምህርት ባለሙያ እና የማሻ ማዕከል አስተባባሪ አቶ አሸናፍ አበበ፤ እንደ ክልል ለመምራን የሙያ ብቃት ምዘና ለመስጠት በርካታ የዝግጅት ስራዎች መካሄዳቸውን ገልፀው በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ለ7 ሺህ 262 መምህራን፣ ለርዕሰ መምራንና ለሱፐርቫይዘሮች ምዘናው አየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ፈተናውን ሲወስዱ ካገኘናቸው መምህራን መካከል መምህር አበበ ፍሰሀና እህታለም አሰፋ እንደተናገሩት፤ ምዘናው ተልዕኮዎቻችንን በብቃትና በሀላፊነት ለመወጣት ያለንበትን አቋም እንድፈትሽና በቀጣይም አቅማችንን እንድናጎለበት የሚረዳ ነው።

በቀጣይም ምዘናው በዓመት ሁለት ጊዜ እንዲደረግና ቀደም ብሎ በፈተናው ዙሪያ የአቅም ግንባታ አጭር ስልጠና እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፡ በዛብህ ታደሰ – ከማሻ ጣቢያችን