የመምህራን የብቃት ማረጋገጫ ምዘና በራሱ የሚተማመን ብቃት ያለው መምህር ለመፍጠር ያለመ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ለመምህራንና ሱፐርቫይዘሮች የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምዘና ተስጥቷል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የትምህርት ልማት ዘርፍ ኃላፊ ታምራት ይገዙ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ የመምህራንና ሱፐርቫይዘሮች የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምዘናው በክልሉ ባሉ በ14 የምዘና ጣቢያዎች 7 ሺህ 2 መቶ 22 መምህራን ምዘናውን ወስደዋል።

አክለውም ምዘናው በአንደኛ፣ በመካከለኛና በሁለተኛ ደረጃ ያሉ መምህራንና ሱፐርቫይዘሮችን ያካተተ ሲሆን ምዘናው ከትምህርት ጥራት አንፃር አሰተዋጽኦው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ለ15 ዓመታት በነበሩ የመምህራን ምዘናዎች አጥጋቢና ከዚያ በላይ ውጤት የሚያመጡ መምህራን ከሚጠበቀው በታች መሆኑን የገለፁት ኃላፊው፤ አሁን ላይ አንድ መምህር የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምዘናውን ተመዝኖ ሲያልፍ ብቻ መምህር መሆኑ ይረጋገጣል በማለት ተናግረዋል።

በተጨማሪም ምዘናው በራሱ የሚተማመን ብቃት ያለው መምህር ለመፍጠርና መምህር የመሆን ያለመሆን ጉዳይ በመሆኑ ምዘናው ለጊዜው በውዴታ እንዲመዘኑ እየተደረገ መሆኑ ተመላክቷል።

ይህም ተመዝኖ ሰርተፊኬቱን የያዘ መምህር በቀጣይ ቅድሚያ የሚሰጠውና የደረጃ እድገትና ሌሎችን ጥቅሞች ጭምር በዚህ ምዘና ውጤት መሰረት የሚያገኙበት ሁኔታ ወደፊት እንደሚኖርም አመላክተዋል።

ክረምት የሚሰጡ ምዘናና ስልጠናዎች ከዚህ የብቃት ማረጋገጫ ምዘና ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌላቸው ኃላፊው ገልፀዋል።

ለምዘናው ዝግጅት እንዲያደርጉ አስቀድሞ የማሳወቅና የመቀስቀስ ሥራ ሲሰራ ቆይቶ ለዛሬ መብቃቱን ገልፀው፤ ከመምህራን መንጠባጠብ ተግዳሮት ውጪ በሠላም መሰጠቱንና ውጤቱም ጥሩ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልፀዋል።

የኣሪ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳግም መኮንን በበኩላቸው፤ የመምህራንን ብቃት በማሻሻል ክፍተቶችን በመለየት ጥራት ያለው መምህር በዞኑ እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።

አስተያየታቸውን ከሰጡን መምህራን መካከል መ/ር ሙስጠፋ እሽቱ፣ ጌጤነሽ ኮልሚ እና ሌሎችም ምዘናው ጥሩና ራሳችንን እንድናይ የሚያስችልና አውቀን እንድናስተምር የሚያስችል ከመሆኑም በላይ የራሳችንን አቅም እንድናሳድግ የሚረዳ ነው ብለዋል።

ዘጋቢ: ከተማ በየነ – ከጂንካ ጣቢያችን