የ2017 ዓ.ም የመምህራን እና የትምህርት አመራር የሙያ ማሻሻያ ምዘና በዲላ ማዕከል እየተሰጠ ነው
በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመምህራን የሚሰጠው የሙያ ማሻሻያ ምዘና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት በዲላ ማዕከል ለ593 መምህራን እና የትምህርት አመራሮች ነው እየተሰጠ ያለው።
የምዘና አሰጣጡን መርሃ ግብር አስመልክተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያ ሀላፊ አቶ ዘማች ክፍሌ፤ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እና የትምህርት ስብራትን ለመጠገን በሙያ የበቁ መምህራን ሊኖሩ ይገባል ብለዋል።
ትውልድን በመቅረጽ ሂደት ውስጥ የመምህር ሚና እጅግ የጎላ ነው ያሉት አቶ ዘማች፤ የሙያ ምዘና ፈተናን መስጠት የተፈለገበት ዋናው ምክንያት የመምህርነት ሙያ ሁልጊዜ ብቃትን የሚጠይቅ በመሆኑ እና መምህሩም በሚያስተምረው የትምህርት ዘርፍ ለራሱ የበቃ መምህርን በመፍጠር ለተማሪዎች የተሻለ እውቀት እንዲመግቡ ታስቦ እንደሆነ ገልፀዋል።
የትምህርት ስራ ከአካዳሚክ እውቀት በተጨማሪ የሙያ እውቀት በማስፈለጉ ምዘናው እንደሚሰጥ እና መምህራን የሚያነሱትን በርካታ ጥያቄዎችን በየደረጃው ለመፍታት ያስችላልም ተብሏል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ የስርዓተ ትምህርት ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ዳዊት ታንጋ እንደገለፁት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተሰጠ ያለው የመምህራን እና የትምህርት አመራር ባለሙያዎች በዲላ ማዕከል በሶስት ፈርጅ ምዘና እየተሰጠ ይገኛል።
ለአንደኛ ደረጃ መምህራን በኤስተቲክስ፣ ልዩ ፍላጎት እና ቋንቋ፤ መለስተኛ እና ለሁለተኛ ደረጃ መምህራን የህብረተሰብ እና የተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት ዓይነቶች ምዘናው እየተሰጠ መሆኑን ነው አቶ ዳዊት ያብራሩት።
በጌዴኦ ዞን ደረጃ 582 የአንደኛ፣ የመለስተኛ እና የሁለተኛ ደረጃ መምህራን እንዲሁም 11 የትምህርት አመራሮች ምዘናውን እየወሰዱ ነው።
ዘጋቢ፡ ወርቅአገኘሁ ወልደየስ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
በ6 ወራት ውስጥ ሊመዘበር የነበረ ከ156 ሚሊየን 560ሺህ ብር በላይ ማዳን መቻሉ ተገለጸ
የጉራጌ ክትፎ ባህልና እውቀትን በዩኒስኮ የሰው ልጆች ወካይ የማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተሰራ እንደሚገኝ የኢፌዲሪ ቅርስ ባለስልጣን ገለፀ
በክልሉ ያሉ ብሔረሰቦችን ባህል ወደፊት በማውጣት የአካባቢውን ሰላምና ልማት ለማስቀጠል በትኩረት መስራት እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳደር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ተናገሩ