የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በጋሞ ዞን በምዕራብ አባያ ወረዳ 31 የኦዲት ግኝቶች ማግኘቱን አስታወቀ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በጋሞ ዞን በምዕራብ አባያ ወረዳ 31 የኦዲት ግኝቶች ማግኘቱን አስታወቀ

የክልሉ ምክር ቤት በወረዳው የታዩ አጠቃላይ የኦዲት ግኝቶች በቀጣይ በአስር ቀናት ውስጥ ታርመው መቅረብ እንዳለባቸው አሳስቧል።

የምዕራብ አባያ ወረዳ ምክር ቤት በበኩሉ ግኝቶችን ለማረም እየተሰራ መሆኑንና በቀጣይ የውስጥ ኦዲት ስራን ማጠናከር ያስፈልጋል ብሏል።

የክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር አቶ አበባየሁ ኤርምያስ፤ በምዕራብ አባያ ወረዳ የመንግስት ሀብትና ንብረት በአግባቡ ስራ ላይ ስለመዋሉ በተሰራው የኦዲት ስራ በ2016 ዓ.ም የከፋ የኦዲት አስተያየት ያገኙ 31 የኦዲት ነቀፌታዎች መታየታቸውን ተናግረዋል።

የአስፈጻሚ አካል ፍቃድ የሌላቸው 270 ምርት መላኪያ ደረሰኞች ታትመው አገልግሎት ላይ መዋላቸው፣ የጨረታ ሂደትን ያልተከተለ ግዥ ማካሄድ፣ ፋክቱር ሳይቀርብ የሚወዳደቁ የነዳጅ ወጪዎችና አላአግባብ የተከፈለ ውሎ አበል በኦዲት ግኝት መገኘቱን ተናግረዋል።

እንዲሁም የግዢ ሂደትን ሳይከተል የወጣ ወጪ መኖሩንና የካሽ ረጂስተር ደረሰኝ ሳይኖር በአታችመንት ብቻ የተወዳደቀ ብር መገኘቱን የገለጹ ሲሆን፤ 7.4 ሚሊዮን ብር ለኦዲት ያልቀረበ ሰነድ መኖሩ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።

የምዕራብ አባያ ወረዳ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍላጎት ባሩዳ ለተነሱ የኦዲት ግኝቶች በሰጡት ምላሽ፤ ህገወጥ ደረሰኝ ህትመቱ በወቅቱ የተመራው በንግድና ገበያ ልማት በመሆኑ የተፈጠረ ክፍተት መሆኑን ጠቅሰው ከግኝቱ በኋላ እርምት ለመውሰድ እንቅስቃሴ ጀምረናል ብለዋል።

የኦዲት ግኝቱ የታየባቸውና በተለይ የካሽ ረጂስተር ሳይኖር በአታችመንት ብቻ የተወዳደቀዉን የሰሩ ባለሙያዎች የዲሲፕሊን እርምጃ እንደተወሰደባቸውና በቀጣይ ግኝቶቾን ለማረም ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

የምዕራብ አባያ ወረዳ ህዝብ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ጦቃ ጮሞርኬ ከደረሰኝ፣ ከውሎ አበልና ከመሳሰሉት ጋር ተያይዞ ህጋዊ አካሄድ አለመኬዱ ግኝቱ እንዲፈጠር ማድረጉንና ግኝቶችን ለማስመለስና ለማረም እንደሚሰራ ገልጸው፤ በቀጣይ የውስጥ ኦዲት ስራን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የክልሉ ዋና ኦዲተር አቶ አበባየሁ ኤርምያስ በማጠቃለያ መልእክታቸው፤ የመንግስት ሀብትና ንብረት በአግባቡ ስራ ላይ እንዲውል ከማድረግ አኳያ የተጠናከረ ስራ ሊሰራ እንደሚገባና ያለው ውስን ሀብት ህግንና አሰራርን በተከተለ መልኩ ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ፕላን መሠረተ ልማትና የመንግስት ሀብት አስተዳደር ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዕንቁ ዮሀንስ በበኩላቸው፤ በኦዲት ግኝት የተያዙ ግኝቶች በፍጥነት ተለይተው ሊታረሙ እንደሚገባና 270 ህጋዊ ያልሆኑት ደረሰኞች አጽንኦት ተሰጥቶ ሊታረሙ እንደሚገባና ስለመታረሙም በቀጣይ መግለጫ መቅረብ እንዳለበት ተናግረዋል።

በወረዳው ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ያልታረሙና የታዩ ግኝቶችን በመልቀም የሚመለሰው ተመልሶ የሚጠየቀው በህግ አግባብ የሚጠየቅበት አሰራር ሊቀመጥ እንደሚገባና ተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳብን በእድሜ ለይቶ በመያዝ ሊሰራ እንደሚገባ የሚገልጹት አቶ እንቁ፤ በቀጣይ የተወሰደውን የእርምት እርምጃ በአስር ቀን ውስጥ ማሳወቅ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን