የንግድ ትርኢትና ባዛሮች ነጋዴዎችንና ሸማቾችን በማቀራረብ ጥራት ያላቸው ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ የሚያስችሉ መሆናቸው ተገለፀ
በጉራጌ ዞን በነጋዴ ሴቶች ማህበር አማካኝነት የተዘጋጀ አረፋን በጉራጌ የንግድ ትርኢት ኤግዚቢሽን እና ባዛር እንዲሁም የባህል ፌስቲቫል በወልቂጤ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አማካሪ አቶ ዳርጌ ተክሉ በመክፈቻ ንግግራቸው እንዳሉት፤ ባዛሩ ከሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባሻገር የህዝብ ለህዝ ግንኙነትን የሚያጠናክር ነው።
የጉራጌ ዞን የነጋዴ ሴቶች አስተባባሪ ወይዘሮ ሮዛ አግዛ አዶት፤ የጉራጌ ነጋዴ ሴቶች ማህበር በ2016 አመተ ምህረት የተቋቋመ ሲሆን በዞኑ ከሚገኙ 8 ሺህ 111 ሴት የነጋዴ ማህበረሰብ ክፍሎችን ያቀፈ ነው ብለዋል።
ማህበሩ በዋናነት አላማ አድርጎ የተነሳው በነጋዴው ማህበረሰብ እና በመንግስት መካከል እንደድልድይ በመሆን ዘርፈ ብዙ ስራዎች እያከናወነ ይገኛልም ሲሉ ተናግረዋል።
መንግስት ለነጋዴ ሴት ማህበራት በአዋጅ ካጎናጸፋቸው መብቶች መካከል አንዱ የንግድ ትርኢት እና ባዛር ማዘጋጀት ነው ያሉት አስተባባሪዋ፤ በዚህም ማህበራቱ የገቢ አቅማቸውን ለማሳደግና የኢኮኖሚ አበርክቷቸውን ለማላቅ እንደሚያስችል አስረድተዋል።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር በበኩላቸው፤ የአረፋ በአልን ምክንያት በማድረግ የንግድ ትርኢትና ባዛር መካሄዱ ሸማቹ ህብረተሰብ ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ የሚያስችለው መሆኑን ተናግረዋል።
ከተማዋን እድሜዋን የሚመጥን ወቅቱን የዋጀ ውብና ማራኪ ገጽታ እንድትላበስ ከማድረግ ጎን ለጎን ኢኮኖሚዋን የማነቃቃት ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ከተለያዩ አቅጣጫዎች መጥተው አገልግሎት አየሰጡ የሚገኙ ነጋዴዎች በበአል ወቅት ማህበረሰቡ የሚፈልጋቸውን የፋብሪካ ምርቶች ይዘው መገኘታቸው ፋይዳው የጎላ ሰለመሆኑም አቶ ሙራድ ገልጸዋል።
ከዚህ ባሻገር ለማህበራዊ መስተጋብር መጠናከር አበርክቶው ከፍተኛ መሆኑንም ከንቲባው አስረድተዋል።
የኦሮሚያ ክልል የነጋዴ ሴቶች የወሊሶ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ሙሉ ዋቃዮ፤ የኦሮሞ እና የጉራጌ ህዝቦች የቀደመ ታሪካዊ ግንኙነት እና የእርስ በርስ ትስስር ያላቸው መሆኑን ጠቁመው ዞኑ በክትፎ ብቻ ሳይሆን በእንግዳ ተቀባይነቱም ይታወቃል ሲሉ ተናግረዋል።
በንግድ ትርኢትና ባዛሩ አግኝተን ያነጋገርናቸው ነጋዴዎች በሰጡት አስተያየት ከአረፋ በአልና ከበአሉም ውጪ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ የኢንደስትሪ ምርቶች የማህበረሰብን የገቢ አቅም ባገናዘበ እና በተመጣጣኝ ዋጋ እየሸጡ መሆኑን ጠቁመዋል
ዘጋቢ፡ አስቻለው አማረ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎችን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሥራ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ገለጹ
የእናቶችንና ጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለፀ
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መስተዳደር (ዶ/ር ) እንዳሻው ጣሰው በተገኙበት በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ምርቃትና የመሰረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ-ስረዓት እየተካሄደ ይገኛል