የከተማዋን ፅዳትና ውበት በዘላቂነት ለመጠበቅ ከመንግሰት ባለፈ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ንቁ ተሳትፎ እንደሚጠይቅ የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር አስታወቀ
በከተማዋ ዛሬ ማለዳ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችን ጨምሮ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የፅዳት ዘመቻ ተካሂዷል፡፡
የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር ሰለሞን ለዊ እንደተናገሩት፤ የከተማዋን ፅዳት በዘላቂነት ለመጠበቅ በመንግሰት አቅም ብቻ ሳይሆን የሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ንቁ ተሳትፎ ያስፈልጋል፡፡
በዚህም የከተማዋ እያንዳንዱ ነዋሪ አካባቢውን በ20 ሜትር ርቀት ፅዳቱን መጠበቅ እንዳለበት አብራርተዋል።
አሁን ላይ በከተማ አስተዳደሩ እየመጣ ያለውን ፈጣን ዕድገትና ለውጥ ይበልጥ ለማስቀጠል የሚያስችሉ ሰፋፊ የአረንጓዴ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ከንቲባው ተናግረዋል፡፡
በተለይ ባለፉት ዓመታት የከተማዋን ፅዳት ለመጠበቅና ህብረተሰቡ የፅዳቱ ባለቤት እንዲሆን በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የገለፁት ከንቲባው፤ በቆሻሻ የተደፈኑ ዲች ቦዮችን በመክፈት የማፅዳት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በየሳምንቱ በሚካሄዱ የፅዳት ንቅናቄ ስራዎች ብቻ የአካባቢ ፅዳት አይጠበቅም ያሉት ከንቲባው፤ ማህበረሰቡ ፅዳትን ባህል አድርጎ የአካባቢን ፅዳት ማስጠበቅ ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
አካባቢያችንን ማፅዳት ብቻ ሳይሆን ዳግም የቆሻሻ መጣያ ቦታ እንዳይሆኑ ነዋሪው በባለቤትነት መጠበቅ ይኖርበታልም ብለዋል::
የከተማ አስተዳደሩ ማዘጋጃ ቤት ዋና ኃላፊ ኢንጂነር በረከት ምናሴ በበኩላቸው፤ በከተማዋ የፅዳት፣ የውበት እና አረንጓዴ ልማት ስራዎች በትኩረት እየተሰሩ ይገኛል ብለዋል።
በከተማዋ ያለውን የቆሻሻ አወጋገድ ስርአት በተገቢው መልኩ መሆን እንዲችልና ብዙሀኑ ያፀዳውን ጥቂቶች ማቆሸሸ ስለማይገባቸው በህግ ተጠያቂ የማድረጉ ተግባር በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ከተማን ፅዱና ውብ ለማድረግና ቆሻሻ የአካባቢን ገፅታ እንዳያበላሽ ለነዋሪው ህብረተሰብ በባለቤትነት እንዲጠብቁ የማስተላለፍ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም አብራርተዋል።
በፅዳት ዘመቻው የተሳተፉ አመራርና የከተማዋ ነዋሪዎችም ከተማዋን ውብና ፅዱ ለኑሮ ምቹ ለማድረግ የተጀመረው ስራ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረው ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በተካሄደው የፅዳት ዘመቻ ላይ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል።
ዘጋቢ፡ ጦያር ይማም – ከሚዛን ጣቢያችን

More Stories
አርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ሳውላ ካምፓስ ለ9ኛ ጊዜ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 121 ተማሪዎችን አስመረቀ
ዲግሪው “ወረቀት ብቻ ሳይሆን፣ የሀገር ተስፋና የትውልድ ኃላፊነት ነው” – አፈወርቅ ካሱ (ፕ/ር)
በክልሉ የተጀመሩ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የድጋፍና ክትትል ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ገለጹ