በናይጄሪያ በደረሰ የጎርፍ አደጋ ከ110 በላይ ሰዎች ህይወት አለፈ
ሀዋሳ፡ ግንቦት 22/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማዕከላዊ ናይጄሪያ የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ሳቢያ የ110 ሰዎች ህይወት መቅጠፉን የአከባቢው ባለስልጣናት ገለጹ፡፡
የዝናብ መጠኑ ለበርካታ ሰዓታት ያለማቋረጥ መጣሉን ተከትሎ ጉዳት ማድረሱን የገለጹት የኒጀር ግዛት የድንገተኛ አደጋ አስተዳደር ኤጀንሲ ኃላፊ አቡላሂ ባባ-አራህ ናቸው።
አክለውም “በጎርፉ ከ50 በላይ መኖሪያ ቤቶች ከነዋሪዎቻቸው ጋር ጭምር በጎርፍ መወሰዳቸውን” ገልጸው፥ በሞክዋ ከተማ ቲፊን ማዛ እና አንጉዋና ሃኡሳዋ ወረዳዎች የከፋ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የሞክዋ ወረዳ ኃላፊ መሀመድ ሻባ አሊዩ በበኩላቸው የዚህ አይነት የጎርፍ አደጋ ሲያጋጥም ከ60 አመታት ወዲህ የመጀመሪያ መሆኑን ጠቁመው፥ የፌደራሉ “መንግስት አስቸኳይ እርዳታ እንዲያቀርብላቸው እማጸናለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
ምንም እንኳ በናይጄሪያ የዝናብ ወቅት መጀመሪያ ቢሆንም በዚህ መጠን ያደረሰው ጉዳት ቀጣዮቹን የዝናብ ጊዜያት በጽኑ አስጊ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
በ2024 ብዙ የሰሜን ናይጄሪያ ክፍሎች ከባድ የዝናብ እና የጎርፍ አደጋ አጋጥሟቸዋል እንደነበረ የሚታወስ ነው ያለው ቢቢሲ፥ ይህም ለሞት፣ ለሰዎች መፈናቀል እና ቤቶች እና መሰረተ ልማቶች ውድመት ማስከተላቸውን ገልጸዋል።
ናይጄሪያ ከዚህ ቀደም እ.ኤ.አ በ2022 ከባድ የጎርፍ አደጋ አጋጥሟት ነበር ያለው ቢቢሲ፥ ይህም ወደ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው በማፈናቀል ከ 600 በላይ ሰዎችን ለሞት ዳርጎ እንደነበር አስታውሷል።
ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ

More Stories
በኮሬ ዞን የአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች መልሶ የማደራጀት ምክክር መድረክ ተካሄደ
በአጋር ድርጅቶች የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች የመንግስት የልማት ክፍተት በመሙላት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ
በሌማት ትሩፋት ከቤት ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን የምዕራብ አባያ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ