የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ውጤታማ መሆናቸው ተገለጸ
በጌዴኦ ዞን የኮቾሬ ወረዳ ምክር ቤት አባላት በወረዳው በክላስተር እየለሙ ያሉ የእንሰትና ቡና ማሳዎች በምክር ቤቱ አባላት ተጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ መረሀ ግብር የኮቾሬ ወረዳ ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አለሙ ዋዩ የህዝቡን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እየተደረገ ያለው ርብርብ አበረታች መሆኑን አንስተው በተለይም በግብርና ሥራዎች የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በቀጣይም ሁሉም በምግብ ራሱን እንዲችል ከማድረጉም ባሻገር ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ ለሀገሪቷ ምጣኔ ሀብት እድገት የበኩሉን የሚወጣ አምራች አርሶ አደር ለማፍራት ከዲላ ዩኒቨርስቲ ምርምር ማዕከል ጋር የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ረገድ ምክር ቤቱ የበኩሉን እንደሚወጣ አፈጉባኤው አስታውቀዋል፡፡
የኮቾሬ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ታሪኩ በበኩላቸው ባለፉት 9 ወራት በወረዳው ዘርፈ ብዙ የልማትና መልካም አስተዳደር ሥራዎች መከናወናቸውን ገልፀው የእንሰትና ቡናን ምርታማነት በመጨመር የአርሶ አደሩን የኑሮ ዘይቤ ለማሻሻል የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል፡፡
በጉብኝቱም በሀንጨቢ ፣ ሲሶታ እና ስጊጋ ክላስተሮች በቡና እና እንሰት እየለማ ያለው ከ1 መቶ 5 በላይ ሄክታር ማሳ የተጎበኘ ሲሆን የበርካቶችን ህይወት የቀጠፈው፣ ለንብረት ውድመት ምክንያት ሆኖ የቆየውና በህብረተሰብ ተሳትፎ እየተገነባ ያለው የመልካላቲ ድልድይ ግንባታ ያለበት ደረጃ በምክር ቤቱ አባላት ተጎብኝተዋል፡፡
አርሶ አደሮች ያረጁና ምርት የማይሰጡ ቡናዎችን በመንቀላቸው ሊገጥማቸው የሚችለውን ጊዜያዊ ችግር ለመቅረፍ ቦሎቄና ሌሎች ቶሎ የሚደርሱ ምርቶችን እያመረቱ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንድያረጋግጡ የዘርና የተፈጥሮ ማዳበሪያ ድጋፍ መደረጉን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው በዞኑ የተሻለ ተሞክሮ ካላቸው አከባቢዎች ልምድ በመቅሰም በእንሰትና ቡና ምርታማነት ላይ የተጀመረውን ሥራ ለማስፋፋት የአርሶ አደሮቹን ግንዛቤ ከፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አክለዋል፡፡
ዘጋቢ ሳሙኤል በቀለ ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
የግል እና የጋራ መጸዳጃ ቤቶችን በተገቢው በመጠቀም ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን አስቀድሞ መከላከል እንደሚገባ በጉራጌ ዞን የእኖር ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት አስገነዘበ
12 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በተቋማት የድርጊት መርሐ-ግብርና በፀደቀላቸው በጀት መሠረት ማሰራጨቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ አስታወቀ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) በምስራቅ ጉራጌ ዞን ቡኢ ከተማ አስተዳደር እየተገነባ የሚገኘውን ብሉ ኤለፋንት ፋይበር ቦርድ ካምፓኒ ጎበኙ