ሁለተኛ ዙር የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ከግንቦት 22 ጀምሮ ለተከታታይ 4 ቀናት እንደሚሰጥ ተገለጸ

ሁለተኛ ዙር የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ከግንቦት 22 ጀምሮ ለተከታታይ 4 ቀናት እንደሚሰጥ ተገለጸ

ሀወሳ፡ ግንቦት 19/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሁለተኛ ዙር የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ከግንቦት 22 ጀምሮ ለተከታታይ 4 ቀናት እንደሚሰጥ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ጤና ፅ/ቤት አስታወቀ።

በሁለተኛ ዙር የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ከ17 ሺህ በላይ ህፃናት እንደሚወስዱ ፅ/ቤቱ ገልጿል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብድልኸይ ኑርሀሰን ለጣቢያችን በሰጡት መግለጫ የልጅነት ልምሻ ሕፃናትን ለሕመም፣ ለአካል ጉዳት እና ለተለያዩ በሽታዎች ከሚዳርጉ በሽታዎች አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአገር አቀፍ፣ በክልል ብሎም በልዩ ወረዳዉ በሽታዉን አስቀድሞ ለመካለከል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

በቀቤና ልዩ ወረዳ በተያዘዉ በጀት አመት የመከላከያ ክትባቱን ከ13 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ህፃናት መሰጠቱን ያነሱት ኃላፊዉ ዉጤታማ እንደነበረም ተናግረዋል።

ከግንቦት 22 ጀምሮ ለተከታታይ 4 ቀናት ለሚሰጠዉ ለሁለተኛ ዙር የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን በመግለፅ ከ17 ሺህ በላይ ህፃናት ክትባቱን እንደሚወስዱ አቶ አብድልኸይ ጠቁመዋል።

ከክትባቱ ጎን ለጎን ሌሎች የጤና ጉዳዮች የህጻናት የምግብ እጥረት ልየታ፣ የመደበኛ ክትባት አገልግሎት ያላገኙና ያቋረጡ ህጻናት ልየታ፣ የማህፀን ዉልቃት ያለባቸዉ እናቶች ልየታ እንደሚደረግም አስረድተዋል።

የሚዲያና የኮምዩንኬሽን አካላት ለስራዉ ዉጤታማነት የበኩላቸዉን አስተዋፆ ማበርከት እንዳለባቸዉና ህብረተሰቡም እድሜያቸዉ ከ59 ወራት በታች የሆኑ ህፃናትን ማስከተብ እንዳለባቸዉ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ሪያድ ሙህዲን – ከወልቂጤ ጣቢያችን